ትንቢተ ኤርምያስ 34
34
ስለ ሴዴቅያስ የተነገረ የትንቢት ቃል
1የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ በግዛቱ ሥር ባሉት መንግሥታትና ሕዝቦች ጭምር እየተረዳ በኢየሩሳሌምና በዙሪያዋ ባሉ ከተሞች ላይ የጦርነት አደጋ በሚጥልበት ጊዜ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናገረኝ። #2ነገ. 25፥1-11፤ 2ዜ.መ. 36፥17-21። 2የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ወደ ይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ ዘንድ ሄጄ እንዲህ ብዬ እንድነግረው አዘዘኝ፤ “እኔ እግዚአብሔር ይህችን ከተማ ለባቢሎን ንጉሥ አሳልፌ እሰጣታለሁ፤ እርሱም በእሳት ያቃጥላታል። 3አንተም ማምለጥ አትችልም፤ ትማረካለህ፤ ለእርሱም ተላልፈህ ትሰጣለህ፤ እርሱን በቀጥታ ፊት ለፊት ታየዋለህ፤ እርሱም ያነጋግርሃል፤ ከዚያም በኋላ ወደ ባቢሎን ትሄዳለህ፤ 4ሴዴቅያስ ሆይ፥ እኔ ስለ አንተ የምለውን ስማ፤ በጦርነት ላይ አትሞትም፤ 5በሰላም ታርፋለህ፤ ከአንተ በፊት ነገሥታት የነበሩ የቀድሞ አባቶችህ በሞቱ ጊዜ ሕዝቡ ለክብራቸው እሳት ያነዱላቸው እንደ ነበር ለአንተም እንዲሁ እሳት ያነዱልሃል፤ ‘ወዮ ንጉሣችን፥’ እያሉም ያለቅሱልሃል፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
6ይህንንም የትንቢት ቃል ለሴዴቅያስ በኢየሩሳሌም በነገርኩት ጊዜ፥ 7የባቢሎን ንጉሥ ሠራዊት በኢየሩሳሌም ከዚያም አልፎ ላኪሽና ዐዜቃ ተብለው በሚጠሩት፥ በይሁዳ ቀርተው በነበሩት የመጨረሻ የተመሸጉ ከተሞች ላይ አደጋ እየጣለ ነበር።
የባሪያ ነጻነት
8የባሪያ ነጻነትን ለማወጅ ሴዴቅያስ ከኢየሩሳሌም ሕዝብ ጋር ተሰብስቦ ስምምነት ካደረገ በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ ወደ ኤርምያስ መጣ። 9ይኸውም ዕብራውያን ባሪያዎቻቸውን በሙሉ ሴቶችንም ወንዶችንም ነጻ ለማውጣት ነበር፤ ማንም ሰው እስራኤላውያን ከሆኑት ወገኖቹ መካከል ባሪያ እንዳይኖረው ወሰኑ። 10ሕዝቡና መሪዎቻቸው ሁሉ ባሪያዎቻቸውን ነጻ ለመልቀቅና እንደገና መልሰውም ባሪያዎች ላለማድረግ ተስማሙ፤ በዚህም ስምምነት መሠረት ሁሉንም ነጻ አወጡአቸው፤ 11ዘግየት ብሎ ግን ሐሳባቸውን ለወጡና በባርነት ያገለገሉአቸው ዘንድ እንደገና ማስገደድ ጀመሩ።
12ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ መጣ፤ 13የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እኔ ራሴ የቀድሞ አባቶቻችሁን ከግብጽ ምድር፥ ከባርነት ቤት ነጻ ባወጣኋቸው ጊዜ ከእነርሱ ጋር እንዲህ ስል ቃል ኪዳን ገብቼ ነበር። 14በዚያም ቃል ኪዳን መሠረት፥ ዕብራውያን ባሪያዎች ያሉአቸው ሁሉ ስድስት ዓመት ካገለገሉአቸው በኋላ በሰባተኛው ዓመት ነጻ እንዲያወጡአቸው አዘዝኩ፤ ነገር ግን የቀድሞ አባቶቻችሁ ሊታዘዙኝም ሆነ ቃሌን ሊሰሙ አልፈለጉም፤ #ዘፀ. 21፥2፤ ዘዳ. 15፥12። 15እነሆ እናንተም ከጥቂት ቀኖች በፊት ተጸጸታችሁ እኔን ደስ የሚያሰኝ ነገር መሥራት ጀምራችሁ ነበር፤ ሁላችሁም ከእስራኤላውያን ወገን የሆኑ ባሪያዎቻችሁን ነጻ ለመልቀቅ ተስማማችሁ፤ እኔ በምመለክበትም ቤተ መቅደስ ተሰብስባችሁ በፊቴ ቃል ኪዳን ገባችሁ፤ 16ነገር ግን እንደገና ሐሳባችሁን በመለወጥ ስሜን የሚያስነቅፍ ሥራ ሠራችሁ፤ ይኸውም ሁላችሁም እንደየፍላጎታቸው ነጻ የለቀቃችኋቸውን እንደገና ባሪያዎች አድርጋችሁ መግዛት ቀጠላችሁ። 17እነሆ እኔ እግዚአብሔር እናንተንም የምላችሁ ይህ ነው፦ ‘አልታዘዛችሁም፤ ወገኖቻችሁ ለሆኑ እስራኤላውያንም ነጻነት አልሰጣችሁም፤’ ስለዚህም እኔ በጦርነት፥ በራብና በወረርሽኝ ትሞቱ ዘንድ እተዋችኋለሁ፤ በእናንተ ላይ በማደርገውም ነገር የዓለም ሕዝብ ሁሉ እንዲሠቀቅ አደርጋለሁ። 18ባሪያዎቻችሁን ነጻ ለማውጣት በፊቴ ቃል ኪዳን በገባችሁ ጊዜ አንድን ጥጃ በመቊረጥ ለሁለት ከፍላችሁ በመካከሉ አልፋችኋል፤ ነገር ግን እናንተ ያን ቃል ኪዳንና እኔም ከእስራኤል ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን አፍርሳችኋል፤ ስለዚህ እናንተ በጥጃው ላይ እንዳደረጋችሁት እኔ በእናንተ ላይ አደርጋለሁ። 19የይሁዳና የኢየሩሳሌምን ታላላቅ ሰዎች፥ የቤተ መንግሥቱን ባለሥልጣኖች፥ ካህናቱንና ተቈርጦ በተከፈለው ጥጃ ብልቶች መካከል ያለፉትን የአገሪቱን ሕዝብ ሁሉ፥ 20ሕይወታቸውን ማጥፋት ለሚፈልጉ ጠላቶቻቸው አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ ሬሳቸውንም ሁሉ የሰማይ ወፎችና የምድር አራዊት ይበሉታል።
21“የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስንና መኳንንቱን ሁሉ ሕይወታቸውን ማጥፋት ለሚፈልጉ ጠላቶቻቸው አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ አሳልፌ የምሰጣችሁም በእናንተ ላይ አደጋ የመጣል ተግባሩን ለገታው ለባቢሎናውያን ሠራዊት ነው።
22“እኔ ትእዛዝ እሰጣለሁ፤ እነርሱም ወደዚህች ከተማ ይመለሳሉ፤ አደጋ ጥለውም በመያዝ ያቃጥሉአታል፤ በይሁዳ የሚገኙ ከተሞችንም ሁሉ ማንም እንደማይኖርበት ባድማ አደርጋቸዋለሁ። እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 34: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997