ትንቢተ ኤርምያስ 33
33
ሌላው አስተማማኝ ተስፋ
1በቤተ መንግሥቱ ግቢ በሚገኘው በዘብ ጠባቂዎች ክፍል ውስጥ ገና ታስሬ እንዳለሁ የእግዚአብሔር ቃል እንደገና መጣልኝ፤ 2ምድርን የፈጠራትና ያዘጋጃት፥ ተደላድላም እንድትኖር ያደረጋት እግዚአብሔር ተናገረኝ፤ ስሙም ጌታ እግዚአብሔር ነው፤ 3እርሱም እንዲህ አለኝ፦ “ጥራኝ፤ እኔም እመልስልሃለሁ፤ ከአሁን በፊት የማታውቃቸውን ተመርምሮ ሊደረሰባቸው የማይችሉትን ታላላቅ ነገሮች እገልጥልሃለሁ። 4በከበባውና በጦርነቱ ጥቃት ምክንያት የኢየሩሳሌም ቤቶችና የይሁዳ ቤተ መንግሥት ይፈራርሳሉ፤ 5ከሕዝቡ መካከል ከባቢሎናውያን ጋር በሚዋጉበት ጊዜ ከክፋታቸው የተነሣ እኔ ፊቴን ከዚህች ከተማ ስላዞርኩ በቊጣዬና በመዓቴ በምገድላቸው ሬሳዎች ቤቶቹ የተሞሉ ይሆናሉ። 6ነገር ግን ይህችን ከተማና ሕዝብዋን እንደገና እፈውሳለሁ፤ ጤንነታቸውንም እመልስላቸዋለሁ፤ በሁሉም ቦታ ሰላምንና የሕይወት ዋስትናን አበዛላቸዋለሁ፤ 7የይሁዳንና የእስራኤልን ምርኮኞች እመልሳለሁ፤ ቀድሞ በነበሩበት ዐይነት እንደገና እመሠርታቸዋለሁ። 8ሕጌን በመጣስ ከፈጸሙት ኃጢአት ሁሉ አነጻቸዋለሁ፤ ኃጢአታቸውንና በዐመፅ የፈጸሙትን ሥራ ሁሉ ይቅር እላለሁ። 9ለኢየሩሳሌም የማደርጋቸውን መልካም ነገሮች ሁሉ በሚሰሙት ሕዝቦች ፊት ለእኔ ገናናነት፥ ክብርና ምስጋናን ታስገኛለች፤ ለኢየሩሳሌም ሕዝብ የማደርገውን መልካም ነገሮችና ለከተማይቱ የማመጣላትን ሀብትና በጎነት በሚሰሙበት ጊዜ አሕዛብ ሁሉ በፍርሃት ይንቀጠቀጣሉ።”
10እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ኤርምያስ ሆይ! ‘ይህች ምድር ሰዎችም ሆኑ እንስሶች የማይኖሩባት ባድማ ነች’ ያልከው አባባል ለጊዜው ትክክል ነው፤ የይሁዳ ከተሞችና የኢየሩሳሌም መንገዶች ምንም ሰዎች ወይም እንስሶች የማይታዩባት ባድማ ነች፤ አንድ ቀን ግን በዚህ ቦታ የተድላና የደስታ ድምፅ ይሰማል፤ 11በዚህ ቦታ የተድላና የደስታ፥ የሠርግ ዘፈን ድምፅ እንደገና ይሰማል፤ ከምርኮ ለተመለሱትም ቀድሞ የነበራቸውን ንብረታቸውን ስለምመልስላቸው የምስጋና መሥዋዕት ለማቅረብ ወደ ቤተ መቅደሴ በሚመጡበት ጊዜ፥ ‘የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ እርሱ ቸር ነውና፥ ፍቅሩም ዘለዓለማዊ ነውና’ እያሉ በከፍተኛ ድምፅ ይዘምራሉ። ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።” #1ዜ.መ. 16፥34፤ 2ዜ.መ. 5፥13፤ 7፥3፤ ዕዝ. 3፥11፤ መዝ. 100፥5፤ 106፥1፤ 107፥1፤ 118፥1፤ 130፥1።
12የሠራዊት አምላክ እንዲህ ይላል፦ “ሕዝብም ሆነ እንስሳ የማይኖርባት ምድረ በዳ በሆነች በዚህች ምድር እንደገና እረኞች የበጎቻቸውን መንጋ የሚያሠማሩበት መስክ ይኖራል። 13በተራራማው አገር በኮረብቶች ግርጌና በይሁዳ ደቡብ ባሉ ከተሞች፥ በብንያም ክፍለ ግዛት፥ በኢየሩሳሌም ዙሪያ ባሉት መንደሮችና በይሁዳ የገጠር ከተሞች ሁሉ እረኞች እንደገና በጎቻቸውን ይቈጥራሉ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
14እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ለእስራኤልና ለይሁዳ ሕዝብ የተስፋ ቃል የምፈጽምበት ጊዜ ተቃርቦአል፤ #ኤር. 23፥5-6። 15በዚያን ጊዜ የዳዊት ዘር ቅርንጫፍ የሆነ አንድ ጻድቅ ንጉሥ እመርጣለሁ፤ ያም ንጉሥ በአገሪቱ ላይ ቅን የሆነውን ነገር ያደርጋል፤ ትክክለኛ ፍርድም ይሰጣል። 16የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ከጠላት እጅ ድነው በሰላም ይኖራሉ። ከተማይቱም ‘እግዚአብሔር ጽድቃችን ነው’ ተብላ ትጠራለች፤ 17ከዳዊት ዘር በእስራኤል ላይ የሚነግሥ ንጉሥ ከቶ እንደማይጠፋ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ፤ #2ሳሙ. 7፥12-16፤ 1ነገ. 2፥4፤ 1ዜ.መ. 1፥11-14። 18እንዲሁም የሚቃጠል መሥዋዕት፥ የእህል መሥዋዕትና ሌላውንም መሥዋዕት በማቅረብ የሚያገለግሉኝ ካህናት ከሌዊ ወገን ከቶ አይጠፉም።” #ዘኍ. 3፥5-10።
19እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ 20-21“ለአገልጋዬ ለዳዊት ዙፋን የሚወርስ ልጅ እንደምሰጠው የገባሁት ቃል ኪዳንና ለአገልጋዮቼ ለሌዋውያን ስለሚሰጡኝ አገልግሎት ያቆምኩላቸው ቃል ኪዳን ሊፈርሱ የሚችሉት ቀንና ሌሊት በተወሰነላቸው ጊዜ እንዲመጡ ያቆምኩላቸውን ሥርዓት ከእናንተ መካከል ለማፍረስ የሚችል ሰው የተገኘ ከሆነው ነው። 22ስለዚህ የአገልጋዬን የዳዊትን ዘርና ከሌዊ ወገን የሆኑትን ካህናት ቊጥር አበዛለሁ፤ ብዛታቸውም ሊቈጠር እንደማይችል እንደ ባሕር አሸዋና እንደ ሰማይ ከዋክብት ይሆናል።”
23እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ 24“እነዚህ ሕዝቦች፦ ‘እግዚአብሔር የመረጣቸውን እነዚያን ሁለት መንግሥታት ትቶአቸዋል’ ብለው ሕዝቤን በመናቅ በሕዝብነት እንደማያውቁአቸው አላስተዋልክምን?” 25ቀጥሎም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “ለቀንና ለሌሊት መፈራረቅ፥ ለሰማይና ለምድር ቋሚ ሥርዓት የሰጠሁበትን ቃል ኪዳን ያልመሠረትሁ ከሆነ፥ 26የያዕቆብና የአገልጋዬን የዳዊትን ዘሮች ትቼአለሁ ማለት ነው፤ ይህም ማለት ለአገልጋዬ ለዳዊት በአብርሃም፥ በይስሐቅና በያዕቆብ ዘሮች ላይ የሚነግሥ አንድም ተወላጅ አላስነሣለትም ማለት ነው። እኔ ግን ምሕረት አደርግላቸዋለሁ፤ ንብረታቸውን እመልስላቸዋለሁ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 33: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997