ትንቢተ ኤርምያስ 1
1
1በብንያም ነገድ ርስት ውስጥ በምትገኝ ዐናቶት በምትባል መንደር ከሚኖሩ ካህናት አንዱ የሆነው የሕልቅያ ልጅ ኤርምያስ የተናገረው ቃል የሚከተለው ነው፤ 2ይህም የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ የመጣው የዐሞን ልጅ ኢዮስያስ በይሁዳ በነገሠ በዐሥራ ሦስተኛው ዓመት ነው። #2ነገ. 22፥3—23፥27፤ 2ዜ.መ. 34፥8—35፥19። 3እንዲሁም የኢዮስያስ ልጅ ኢዮአቄም በነገሠበት ዘመንና፥ ከዚያም በኋላ የኢዮስያስ ልጅ ሴዴቅያስ ነግሦ ዐሥራ አንድ ዓመት እስከሆነው ድረስ ማለት በዚያው ዓመት በአምስተኛው ወር የኢየሩሳሌም ሕዝብ ተማርኮ እስከ ተወሰደ ድረስ የእግዚአብሔር ቃል በኤርምያስ አማካይነት ተነግሮአል። #2ነገ. 23፥36—24፥7፤ 24፥18—25፥21፤ 2ዜ.መ. 36፥5-8፤ 11፥21።
የኤርምያስ መጠራት
4የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦ 5“ኤርምያስ ሆይ! ገና በእናትህ ማሕፀን እንድትፀነስ ከማድረጌ በፊት ዐውቄሃለሁ፤ ከመወለድህም በፊት አንተን በመለየት ለሕዝቦች ነቢይ አድርጌ ሾሜሃለሁ።”
6እኔም፥ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! ገና ልጅ ስለ ሆንኩ እንዴት እንደምናገር አላውቅም” ብዬ መለስኩለት።
7እግዚአብሔር ግን እንዲህ አለኝ፦ “ ‘ገና ልጅ ነኝ’ አትበል፤ የምትሄደው እኔ ወደምልክህ ቦታ ነው፤ የምትናገረውም እኔ የማዝህን ሁሉ ነው፤ 8እኔ ከአንተ ጋር ሆኜ ስለምታደግህ እነርሱን ከቶ አትፍራቸው፤ ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ!”
9ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር እጁን ዘርግቶ ከንፈሮቼን ዳሰሰ፤ እንዲህም አለኝ፦ “እነሆ የምትናገረውን ቃሌን ሰጥቼሃለሁ፤ 10እነሆ መንቀልና ማፍረስ፥ ማጥፋትና መገለባበጥ፥ ማነጽና መትከል እንድትችል በአሕዛብና በመንግሥታት ላይ ሥልጣን ሰጥቼሃለሁ።”
ነቢዩ ያያቸው ሁለት ራእዮች
11እግዚአብሔርም “ኤርምያስ ሆይ! የምታየው ነገር ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀኝ።
እኔም “የለውዝ ቅርንጫፍ አያለሁ” አልኩት።
12እግዚአብሔርም “በትክክል አይተሃል፤ እኔም እንዲሁ ቃሌ እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆን አተኵሬ እመለከታለሁ” አለኝ።
13እንደገናም እግዚአብሔር “ሌላስ የምታየው ነገር ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀኝ።
እኔም “በስተ ሰሜን በኩል አንድ ማሰሮ ሲፈላ አያለሁ፤ ወደዚህም ለመገልበጥ አዘንብሎአል” ስል መለስኩለት።
14እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ “በስተ ሰሜን በኩል ጥፋት ገንፍሎ በዚህች ምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ ይከነበልባቸዋል፤ 15በስተ ሰሜን የሚኖሩ ሕዝቦች ወደዚህ እንዲመጡ እጠራለሁ፤ ኢየሩሳሌምንና በዙሪያዋ ያሉትን የይሁዳ ከተሞች አደጋ ጥለው ይይዙአቸዋል፤ ከዚያም በኢየሩሳሌም መግቢያ በር ላይ ዙፋናቸውን ይዘረጋሉ። 16ሕዝቤ ኃጢአት ስለ ሠሩ እቀጣቸዋለሁ፤ እነርሱ እኔን ትተው ለሌሎች አማልክት ዕጣን ያጥናሉ፤ ምስሎችንም ሠርተው ይሰግዱላቸዋል። 17ስለዚህ ኤርምያስ ሆይ! እኔ የማዝህን ሁሉ እንድትነግራቸው ወደ እነርሱ ለመሄድ ተዘጋጅ፤ እነሆ እነርሱን አትፍራ፤ አለበለዚያ በእነርሱ ፊት የበለጠ እንድትፈራ አደርግሃለሁ። 18-19ኤርምያስ ሆይ! እነሆ አድምጠኝ! በዚህ ምድር የሚኖሩ ሁሉ፥ ይህም ማለት የይሁዳ ነገሥታት ባለሥልጣኖች፥ ካህናቱና ሕዝቡም ሳይቀሩ በአንተ ላይ በጠላትነት ይነሡብሃል፤ ይሁን እንጂ እነርሱን ለመቋቋም የሚያስችልህን ኀይልና ብርታት እሰጥሃለሁ፤ እንደ ተመሸገች ከተማ፥ እንደ ብረት ምሰሶና ከነሐስ እንደ ተሠራ ግንብ ጠንካራ አደርግሃለሁ፤ እኔ ከአንተ ጋር ሆኜ በመጠበቅ ስለምከላከልልህ እነርሱ ከቶ ሊያሸንፉህ አይችሉም፤ ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 1: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997