ከዚህ በኋላ የኤፍሬም ሰዎች ጌዴዎንን “ምድያማውያንን ለመውጋት ስትሄድ እኛን ለምን አልጠራኸንም? በእኛ ላይ ለምን እንዲህ አደረግህ?” ሲሉ በምሬት ወቀሱት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፤ “እኔ ካደረግሁት እናንተ ያደረጋችኹት አይበልጥምን? የእኔ ጐሣ በሙሉ ከሠራው ሥራ የኤፍሬም ሰዎች የሠራችሁት ጥቂቱ ሥራ ይበልጣል። የኤፍሬም ወይን ቃርሚያ ከአቢዔዜር ወይን መከር አይሻልምን? እግዚአብሔር የምድያማውያንን መሪዎች ገድላችሁ ድልን እንድትቀዳጁ አድርጓችኋል። ታዲያ እኔ ከዚህ ጋር የሚወዳደር ምን ሠራሁ?” እርሱም ይህን ባለ ጊዜ ቊጣቸው በረደ። በዚህም ጊዜ ጌዴዎንና የእርሱ ሦስት መቶ ሰዎች ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ መጥተው ተሻገሩ፤ ድካም ቢሰማቸውም እንኳ አሁንም ጠላትን በማሳደድ ላይ ነበሩ። ወደ ሱኮት በደረሱም ጊዜ ጌዴዎን ለከተማይቱ ሰዎች እንዲህ አለ፤ “እስቲ ለሰዎቼ እንጀራ ስጡልኝ፤ እነርሱ እጅግ ደክመዋል፤ እኔም ዜባሕና ጻልሙናዕ የተባሉትን የምድያማውያን ነገሥታት በማሳደድ ላይ ነኝ።” የሱኮት መሪዎች ግን “ለአንተ ሠራዊት ምግብ የምንሰጠው በምን ምክንያት ነው? ዜባሕንና ጻልሙናዕን ገና አልማረክህም” አሉት። ጌዴዎንም “ደግ ነው! እግዚአብሔር በዜባሕና በጻልሙናዕ ላይ ድልን በሚያጐናጽፈኝ ጊዜ ከበረሓ በሚገኙ እሾኽና አሜከላ እገርፋችኋለሁ!” አላቸው። ጌዴዎን ወደ ጵኑኤልም ሄዶ በዚያ የሚኖሩትን ሰዎች ያንኑ ጥያቄ አቀረበላቸው፤ ነገር ግን የጵኑኤልም ሰዎች የሱኮት ሰዎች የሰጡትን ተመሳሳይ መልስ ሰጡት። ስለዚህ እነርሱንም “ድልን ተቀዳጅቼ በሰላም እመለሳለሁ፤ በዚያን ጊዜ የከተማ መጠበቂያ ግንባችሁን አፈርሳለሁ” አላቸው። ዜባሕና ጻልሙናዕ ከምሥራቅ ሠራዊት ከተረፉት ዐሥራ አምስት ሺህ ወታደሮቻቸው ጋር በቃርቆር ነበሩ፤ አንድ መቶ ኻያ ሺህ መሣሪያ የታጠቁ ወንዶች አልቀው ነበር። ስለዚህ ጌዴዎን በበረሓው መንገድ አድርጎ በኖባሕና በዮግበሃ ምሥራቅ በኩል ወጣና የጠላት ሠራዊት ሳያስበው በመዝናናት ላይ እያለ አደጋ ጣለበት። ሁለቱ የምድያማውያን ነገሥታት ዜባሕና ጻልሙናዕ ሸሹ፤ ነገር ግን ጌዴዎን አሳዶ ማረካቸው፤ ሠራዊታቸውንም በሙሉ በድንጋጤ ላይ እንዲወድቁ አደረገ። የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎን በሔሬስ ዳገት በኩል ከጦርነት ተመለሰ፤ ከሱኮትም ሰዎች አንዱን ወጣት ይዞ መረመረው፤ ወጣቱም የሱኮትን መሪዎችና ሽማግሌዎች የነበሩትን የሰባ ሰባት ሰዎችን ስም ዝርዝር ጽፎ ሰጠው። ከዚህ በኋላ ጌዴዎን ወደ ሱኮት ሰዎች መጥቶ “ ‘ዜባሕንና ጻልሙናዕን ገና አልማረክህም፤ ታዲያ አሁን በረሀብ ለደከሙት ወታደሮችህ ምግብ የምንሰጠው ለምንድን ነው?’ ብላችሁ አሹፋችሁብኝ ነበር፤ አሁን ግን ዜባሕና ጻልሙናዕ እነሆ በእጄ ይገኛሉ!” አላቸው። ከዚህ በኋላ እሾኽና አሜከላ ከበረሓ ወስዶ የሱኮትን መሪዎች ገረፋቸው። በጵኑኤል ያለውንም የከተማ መጠበቂያ ግንብ አፈረሰ፤ በከተማይቱ ውስጥ የሚገኙትንም ወንዶች ሁሉ ገደለ። ከዚህ በኋላ ጌዴዎን “በታቦር የገደላችኋቸው ሰዎች እንዴት ያሉ ነበሩ?” ሲል ዜባሕንና ጻልሙናዕን ጠየቀ። እነርሱም “አንተን ይመስሉ ነበር፤ እያንዳንዳቸው የንጉሥ ልጅ ይመስላሉ” አሉት። ጌዴዎንም “እነርሱ የእናቴ ልጆች ወንድሞቼ ነበሩ፤ እናንተ እነርሱን ባትገድሉ ኖሮ እኔም ምሕረት አደርግላችሁ እንደ ነበር በእርግጥ እምላለሁ” አላቸው። ከዚህ በኋላ የበኲር ልጁን ዬቴርን “በል አሁን ግደላቸው!” ብሎ አዘዘው። ልጁ ግን ሰይፉን ሳይመዝ ቀረ፤ ገና ልጅ ስለ ነበር አመነታ። ከዚህ በኋላ ዜባሕና ጻልሙናዕ ጌዴዎንን “በል እንግዲህ አንተው ራስህ ግደለን፤ የሰው ኀይሉ እንደ ሰውነቱ ነው” አሉት፤ ስለዚህ ጌዴዎን እነርሱን ገድሎ በግመሎቻቸው አንገት ላይ የነበረውን ጌጣጌጥ በሙሉ ወሰደ። ከዚህ በኋላ እስራኤላውያን ጌዴዎንን “አንተ ከምድያማውያን እጅ አድነኸናልና አንተና ከአንተም በኋላ ልጆችህ እንዲሁም የልጅ ልጆችህ ገዢዎቻችን ሁኑ፤” አሉት። ጌዴዎንም “እኔም ሆንኩ ልጄ የእናንተ ገዢዎች አንሆንም፤ የእናንተ ገዢ ራሱ እግዚአብሔር ነው” ሲል መለሰላቸው። እስማኤላውያን የጆሮ ጉትቻ ማድረግ ልማዳቸው ስለ ነበረ የጌዴዎን ወታደሮች ጉትቻዎቻቸውን ማርከው ነበር፤ ጌዴዎንም “እያንዳንዳችሁ የማረካችሁትን ጉትቻ ስጡኝ” ብሎ ለመናቸው። ሕዝቡም “በደስታ እንሰጥሃለን” አሉት። ልብስ አንጥፈውም እያንዳንዱ የወሰደውን የጆሮ ጒትቻ በዚያ ላይ አኖረ። ጌዴዎን የተቀበለው የጆሮ ጒትቻ ኻያ ኪሎ ያኽል የሚመዝን ሆነ፤ ይህም ሌላውን ጌጣጌጥ፥ የአንገት ሐብልና የምድያማውያን ነገሥታት ይለብሱት የነበረውን ሐምራዊ ልብስ፥ እንዲሁም በግመሎቻቸው አንገት ዙሪያ ያለውን ጌጥ ሳይጨምር ነው። ጌዴዎንም ከዚያ ወርቅ ጣዖት ሠርቶ በትውልድ ከተማው በዖፍራ አኖረው፤ እስራኤላውያንም በሙሉ ከእግዚአብሔር ተለይተው ያንን ማምለክ ጀመሩ፤ ለጌዴዎንና ለቤተሰቡ ሁሉ መሰናከያ ወጥመድ ሆነ። በዚህ ዐይነት ምድያም በእስራኤላውያን ተሸነፈች፤ ዳግመኛም ለእስራኤላውያን የምታሰጋ አልሆነችም፤ ጌዴዎን እስከ ሞተም ድረስ በምድሪቱ ላይ አርባ ዓመት ሙሉ ሰላም ሆነ። የኢዮአስም ልጅ ጌዴዎን ወደ ተወለደበት ቦታ ሄዶ በቤቱ ተቀመጠ። ብዙ ሚስቶች ስላገባ ሰባ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ በሴኬም የምትኖርም ቊባት ነበረችው፤ እርስዋም ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ስሙንም አቤሜሌክ ብሎ ጠራው። የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎን ዕድሜ ጠግቦ ሞተ፤ በአባቱም በኢዮአስ መቃብር ተቀበረ፤ ይህም መቃብር የአቢዔዜር ጐሣ ከተማ በነበረችው በዖፍራ ይገኛል። ጌዴዎን ከሞተ በኋላ የእስራኤል ሕዝብ እንደገና ለእግዚአብሔር ያላቸውን ታማኝነት አጓድለው በዓሊም የተባሉትን ባዕዳን አማልክት አመለኩ፤ ለባዓልበሪትም ሰገዱ። የእስራኤልም ልጆች በዙሪያቸው ከነበሩት ጠላቶቻቸው ሁሉ ያዳናቸውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን ረሱ። ለእስራኤል ያደረገውን መልካም ነገር ሁሉ ካለማስታወሳቸው የተነሣ ለጌዴዎን ቤተሰብ ባለ ውለታዎች ሆነው አልተገኙም።
መጽሐፈ መሳፍንት 8 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ መሳፍንት 8:1-35
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos