በዚህ ጊዜ የኤፍሬም ሰዎች፣ “ምድያማውያንን ለመውጋት ስትሄድ ለምን አልጠራኸንም? ለምንስ እንዲህ ያለ ነገር አደረግህ?” በማለት ጌዴዎንን እጅግ ነቀፉት። ጌዴዎን ግን፣ “እናንተ ካደረጋችሁት ጋር ሲነጻጸር የእኔ ከምን ይቈጠራል? የኤፍሬም የወይን ቃርሚያ ተጠቃሎ ከገባው ከአቢዔዝር የወይን መከር አይበልጥምን? እግዚአብሔር የምድያማውያንን መሪዎች ሔሬብንና ዜብን በእጃችሁ አሳልፎ ሰጣችሁ፤ ታዲያ እናንተ ከፈጸማችሁት ጋር የሚወዳደር ምን ማድረግ እችል ነበር?” ይህን ሲሰሙ ቍጣቸው በረደ። ጌዴዎንና ሦስት መቶዎቹ ሰዎች ዮርዳኖስን ተሻገሩ፤ ምንም እንኳ ድካም ቢሰማቸውም ጠላቶቻቸውን ያሳድዱ ነበር። የሱኮትንም ሰዎች፣ “የምድያምንም ነገሥታት ዛብሄልንና ስልማናን በማሳደድ ላይ ስለሆንሁ የተከተሉኝም ሰዎች ስለ ደከሙብኝ እባካችሁ የሚበሉትን እንጀራ ስጧቸው” አላቸው። የሱኮት ሹማምት ግን፣ “ለተከተሉህ ሰዎች እንጀራ እንሰጥ ዘንድ ዛብሄልና ስልማና በእጅህ ገብተዋልን?” አሉት። ጌዴዎንም መልሶ፣ “ደኅና፤ እግዚአብሔር ዛብሄልንና ስልማናን በእጄ አሳልፎ በሚሰጥበት ጊዜ በምድረ በዳ እሾኽና አሜከላ ሥጋችሁን እተለትላለሁ” አላቸው። ከዚያም ወደ ጵኒኤል ሰዎች ሄዶ ያንኑ ጥያቄ አቀረበላቸው፤ የእነርሱም መልስ የሱኮት ሰዎች ከሰጡት መልስ ጋር አንድ ዐይነት ነበር። እርሱም የጵኒኤልን ሰዎች፣ “በድል አድራጊነት በሰላም ስመለስ ከተማችሁን የምትጠብቁበትን ይህን ግንብ አፈርሰዋለሁ” አላቸው። በዚህ ጊዜ ዛብሄልና ስልማና ዐሥራ አምስት ሺሕ ከሆነ ሰራዊታቸው ጋር ቀርቀር በተባለ ስፍራ ነበሩ፤ ይህም ከምሥራቅ ሕዝቦች ከተውጣጣውና በጦር ሜዳ ከወደቀው መቶ ሃያ ሺሕ ሰይፍ ታጣቂ ሰራዊት የተረፈው ነበር። ከዚያም ጌዴዎን ተነሣ፤ ከኖባህና ከዮግብሃ በስተ ምሥራቅ የሚኖሩ ዘላኖች የሚሄዱበትን መንገድ ተከትሎ በጠላት ሰራዊት ላይ በድንገት አደጋ ጣለ። ሁለቱ የምድያም ነገሥታት ዛብሄልና ስልማና ሸሹ፤ ጌዴዎን ግን አሳድዶ ያዛቸው፤ መላ ሰራዊታቸውንም እጅግ በታተነው። ከዚህ በኋላ የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎን በሐሬስ መተላለፊያ በኩል አድርጎ ከጦርነቱ ተመለሰ፤ እርሱም የሱኮት ሰው የሆነ አንድ ወጣት ማረከ፤ መረመረውም፤ ወጣቱም የሰባ ሰባት የሱኮት ሹማምትና የከተማዪቱንም አለቆች ስም ጻፈለት። ከዚያም ጌዴዎን ወደ ሱኮት ሰዎች መጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “ ‘ለደከሙት ሰዎችህ እንጀራ እንሰጥ ዘንድ ዛብሄልና ስልማና በእጅህ ገብተዋልን’ በማለት ያላገጣችሁብኝ ዛብሄልና ስልማና እነዚሁላችሁ።” ጌዴዎን የከተማዪቱን አለቆች ወሰደ፤ በምድረ በዳ እሾኽና አሜኬላ በመቅጣት የሱኮትን ሰዎች ትምህርት ሰጣቸው። እንዲሁም በጵኒኤል ያለውን የከተማ መጠበቂያ ግንብ አፈረሰ፤ የከተማዪቱንም ሰዎች ገደለ። ዛብሄልና ስልማናንም፣ “በታቦር ላይ የገደላችኋቸው ሰዎች እንዴት ያሉ ነበሩ?” በማለት ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “ሁሉም እንዲህ እንደ አንተ ያሉ የንጉሥ ልጆች የሚመስሉ ናቸው” አሉት። ጌዴዎንም፣ “እነርሱ የእናቴ ልጆች ወንድሞቼ ናቸው፤ ባትገድሏቸው ኖሮ እኔም እንደማልገድላችሁ በሕያው እግዚአብሔር ስም አረጋግጥላችሁ ነበር።” ብሎ መለሰላቸው። ከዚያም ወደ በኵር ልጁ ወደ ዮቴር ዘወር ብሎ፣ “ግደላቸው” አለው፤ ዮቴር ግን ትንሽ ልጅ ነበርና ስለ ፈራ ሰይፉን አልመዘዘም። ዛብሄልና ስልማናም፣ “የሰው ጕልበቱ እንደ ሰውነቱ መጠን ነውና አንተው ራስህ ግደለን” አሉት፤ ጌዴዎንም ተነሥቶ ገደላቸው፤ በግመሎቻቸው ዐንገት ላይ የነበሩትንም ጌጦች ወሰደ። እስራኤላውያንም ጌዴዎንን፣ “ከምድያማውያን እጅ ታድገኸናልና አንተ፣ ልጅህና የልጅ ልጅህ ግዙን” አሉት። ጌዴዎን ግን መልሶ፣ “እኔም ሆንሁ ልጄ አንገዛችሁም፤ የሚገዛችሁ እግዚአብሔር ነው” አላቸው። እርሱም፣ “አንድ የምጠይቃችሁ ነገር አለኝ፤ ይኸውም እያንዳንዳችሁ ከምርኮ ካገኛችሁት ውስጥ የጆሮ ጕትቻችሁን እንድትሰጡኝ ነው” አላቸው፤ የወርቅ ጕትቻ ማድረግ የእስማኤላውያን ባህል ነበርና። እነርሱም መልሰው፤ “ደስ እያለን እንሰጥሃለን” አሉት፤ ወዲያው ልብስ አነጠፉ፤ በላዩም ላይ እያንዳንዳቸው ከማረኩት ውስጥ የጆሮ ጕትቻ ጣል ጣል አደረጉለት። ሌሎቹን ጌጣጌጦች፣ ይኸውም የዐንገት ሐብሉን ከነ እንጥልጥሉ፣ የምድያም ነገሥታት ይለብሱት የነበረውን ሐምራዊ ልብስ ወይም በግመሎቻቸው ዐንገት ላይ ያሉትን ጌጦች ሳይጨምር ጌዴዎን በጠየቃቸው መሠረት የሰጡት የወርቅ ጕትቻ ክብደት ሺሕ ሰባት መቶ ሰቅል ያህል መዘነ። ጌዴዎን በወርቁ ኤፉድ ሠራ፤ በተወለደበትም ከተማ በዖፍራ አኖረው። እስራኤልም በሙሉ ኤፉዱን በማምለክ ስላመነዘሩ፣ ኤፉዱ ለጌዴዎንና ለቤተ ሰቡ ወጥመድ ሆነ። ስለዚህ ምድያማውያን በእስራኤላውያን ተሸነፉ፤ ዳግመኛም ራሳቸውን ከፍ ከፍ አላደረጉም። ጌዴዎን በሕይወት እስካለ ጊዜ ድረስ ምድሪቱ አርባ ዓመት ሰላም አገኘች። የኢዮአስ ልጅ ይሩባኣል ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ በዚያም ተቀመጠ። ብዙ ሚስቶች ስላገባ ሰባ ልጆች ነበሩት፤ በሴኬም የምትኖረው ቁባቱም እንደዚሁ ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ስሙንም አቤሜሌክ አለው። የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎን ዕድሜ ጠግቦ ሞተ፤ በአቢዔዝራውያን ምድር ባለችው በዖፍራ፣ በአባቱ በኢዮአስ መቃብር ተቀበረ። ጌዴዎን ሞቶ ብዙም ሳይቈይ እስራኤላውያን የበኣልን አማልክት በማምለክ አመነዘሩ፤ በኣልብሪትንም አምላካቸው አደረጉ፤ በዙሪያቸው ከነበሩት ጠላቶቻቸው እጅ የታደጋቸውን እግዚአብሔር አምላካቸውን አላሰቡትም። እንዲሁም ይሩባኣል የተባለው ጌዴዎን ያደረገላቸውን በጎ ነገር ሁሉ አስበው ለቤተ ሰቡ ውለታ መላሽ ሆነው አልተገኙም።
መሳፍንት 8 ያንብቡ
ያዳምጡ መሳፍንት 8
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መሳፍንት 8:1-35
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos