የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መሳፍንት 6:33-40

መጽሐፈ መሳፍንት 6:33-40 አማ05

ከዚያም በኋላ ምድያማውያን፥ ዐማሌቃውያንና የምሥራቅ ሰዎች በአንድነት ተሰብስበው የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻገሩ፤ በኢይዝራኤል ሸለቆም ሰፈሩ። የእግዚአብሔር መንፈስ በጌዴዎን ላይ ወረደ፤ የአቢዔዜር ጐሣ ሰዎች ሁሉ እንዲከተሉት እነርሱን ለመጥራት እምቢልታ ነፋ፤ የምናሴን ነገድ ሁሉ መልእክት ልኮ ይከተሉት ዘንድ አስጠራቸው፤ እንዲሁም ወደ አሴር፥ ወደ ዛብሎንና ወደ ንፍታሌም ነገዶች መልእክተኞች ላከ፤ እነርሱም ከሌሎቹ ጋር ለመሰለፍ ወጡ። ከዚህ በኋላ ጌዴዎን እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፦ “እንደ ተናገርከው እስራኤልን በእኔ እጅ ታድን ዘንድ መርጠኸኛል። እነሆ! ስንዴ በምንወቃበት አውድማ ላይ የተባዘተ የበግ ጠጒር አስቀምጣለሁ፤ ነገ ጧት ሌላው ምድር ሁሉ ደረቅ ሆኖ በዚህ ጠጒር ባዘቶ ላይ ብቻ ጤዛ ከሆነ፥ እንደ ተናገርከው እስራኤልን ለማዳን የመረጥከኝ መሆኑን አረጋግጣለሁ።” ልክ እርሱ እንዳለውም ሆነለት፤ ጌዴዎን ጧት በማለዳ በተነሣ ጊዜ የበግ ጠጒሩን ባዘቶ ሲጨምቀው በአንድ መቅጃ የሚሞላ ውሃ ከውስጡ ወጣ። ቀጥሎም ጌዴዎን እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፤ “እባክህ አትቈጣኝ፤ እንደገና አንድ ጊዜ እንድናገር ፍቀድልኝ፤ ይኸውም በበግ ጠጒሩ ባዘቶ ላይ ሌላ ምልክት እንዲታይ ልጠይቅ፤ በዚህን ጊዜ የጠጒሩ ባዘቶ ደረቅ ሆኖ በዙሪያው ያለው ምድር እርጥብ እንዲሆን አድርግልኝ።” በዚያን ሌሊት እግዚአብሔር ያንኑ ምልክት አደረገ፤ በማግስቱ ጧት የጠጒሩ ባዘቶ ደረቅ ሆኖ በዙሪያው ያለው መሬት ግን በጤዛ ርሶ ተገኘ።