የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መሳፍንት 2:6-23

መጽሐፈ መሳፍንት 2:6-23 አማ05

ኢያሱ ሕዝቡን ባሰናበተ ጊዜ እስራኤላውያን ሁሉ የየራሳቸውን ድርሻ ለመያዝ ወደየተመደበላቸው ርስት ሄዱ። በኢያሱ ዘመንና በኋላ እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ ያደረገውን ታላቅ ሥራ ባዩት ሽማግሌዎች የሕይወት ዘመን ሁሉ ሕዝቡ እግዚአብሔርን አመለከ። የእግዚአብሔር አገልጋይ የነዌ ልጅ ኢያሱ ዕድሜው መቶ ዐሥር ዓመት ሲሆነው ሞተ፤ የራሱ ድርሻ በሆነውም ርስት ተቀበረ፤ ይህም እርሱ የተቀበረበት ምድር በኮረብታማው የኤፍሬም አገር ከጋዓሽ ተራራ በስተሰሜን የሚገኘውና “ቲምናት ሴራሕ” ተብሎ የሚጠራው ነው። ያ ትውልድ በሙሉ ሞተ፤ ከዚያ ቀጥሎ እግዚአብሔርንና ለእስራኤል ያደረገውን መልካም ነገር የማያውቅ ሌላ ትውልድ ተነሣ። ከዚህ በኋላ የእስራኤል ሕዝብ ክፉ ሥራ በመሥራት እግዚአብሔርን በደሉ። በዓሊም ተብለው የሚጠሩትን ባዕዳን አማልክት አመለኩ፤ ከግብጽ ያወጣቸውን የቀድሞ አባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ማገልገል ተዉ፤ በዚህም ፈንታ በዙሪያቸው ያሉ ሕዝቦች የሚያመልኩአቸውን የውሸት አማልክትን ማገልገል ጀመሩ፤ ለእነርሱም በመስገድ እግዚአብሔርን አስቈጡት። እግዚአብሔርን ማምለክ ትተው “ባዓልና ዐስታሮት” ተብለው የሚጠሩትን ባዕዳን አማልክት አመለኩ፤ ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ በጣም ተቈጣ፤ እንዲዘርፉአቸውም ለወራሪዎች አሳልፎ ሰጣቸው፤ በዙሪያቸው ያሉ ጠላቶቻቸውም እንዲበረቱባቸው አደረገ። ከዚያም በኋላ እስራኤላውያን ከጠላቶቻቸው ወረራ ራሳቸውን መከላከል ተሳናቸው። ወደ ጦርነት በሄዱም ቊጥር ቀደም ብሎ በመሐላ በተናገረው መሠረት እግዚአብሔር ራሱ ይቃወማቸው ነበር፤ ከዚህም የተነሣ እነርሱ በብርቱ ጭንቀት ላይ ወደቁ። ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ከወራሪዎቻቸው እጅ የሚያድኑአቸውን መሳፍንት ተብለው የሚጠሩ መሪዎችን አስነሣላቸው። ነገር ግን የእስራኤል ሕዝብ ለመሪዎቻቸው የማይታዘዙ ሆኑ፤ ለእግዚአብሔርም ያላቸውን ታማኝነት አጓድለው የሌሎች ባዕዳን አማልክት አገልጋዮች ሆኑ፤ አባቶቻቸው የእግዚአብሔርን ትእዛዞች ያከብሩ ነበር፤ እነርሱ ግን የአባቶቻቸውን ምሳሌ አልተከተሉም። እግዚአብሔር መስፍን ባስነሣላቸው ጊዜ ሁሉ እርሱ ከመስፍኑ ጋር ነበር፤ በሚያሳድዱአቸውና በሚጨቊኑአቸው ጠላቶች ምክንያት ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር በሚጮኹበት ጊዜ እግዚአብሔር ያዝንላቸው ስለ ነበረ በመስፍኑ ዘመን ሁሉ ከጠላቶቻቸው እጅ ያድናቸው ነበር። ነገር ግን መሪ በሚሞትበት ጊዜ ሁሉ ተመልሰው ሌሎች አማልክትን በመከተል፥ ለእነርሱም በመስገድና እነርሱንም በማምለክ ከአባቶቻቸው የከፋ በደል ይፈጽሙ ነበር፤ መጥፎ ድርጊታቸውንና ልበ ደንዳና መሆናቸውን አልተዉም። ስለዚህ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ እጅግ ተቈጥቶ እንዲህ አለ፦ “ይህ ሕዝብ ከአባቶቹ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን አፈረሰ፤ ትእዛዜን አልጠበቀም። ስለዚህ ኢያሱ በሞተ ጊዜ በምድሪቱ የነበሩትን ሰዎች አንዳቸውንም አላስወጣላቸውም። እንዲያውም እነዚህ የእስራኤል ሕዝብ እንደ ቀድሞ አባቶቻቸው መንገዴን ይከተሉ ወይም አይከተሉ እንደሆን የማውቀው በእነዚህ ሕዝቦች መሣሪያነት በመፈተን ነው።” ስለዚህ እግዚአብሔር ለኢያሱ አሳልፎ በመስጠት እነዚያን ሕዝቦች በአንድ ጊዜ አላስወጣቸውም።