የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መሳፍንት 2:6-23

መሳፍንት 2:6-23 NASV

ኢያሱ ሕዝቡን ካሰናበተ በኋላ እያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ ምድሪቱን ለመውረስ ወደየርስቱ ሄደ። ኢያሱ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ እንዲሁም ከርሱ በኋላ እግዚአብሔር ለእስራኤል ያደረገውን ታላላቅ ነገሮች ሁሉ ያዩ አለቆች በነበሩበት ዘመን ሁሉ ሕዝቡ እግዚአብሔርን አመለከ። የእግዚአብሔር አገልጋይ የነዌ ልጅ ኢያሱ በመቶ ዐሥር ዓመቱ ሞተ። እነርሱም በኰረብታማው በኤፍሬም አገር በምትገኘው ከገዓስ ተራራ በስተሰሜን ባለችው በራሱ ርስት ላይ በተምናሔሬስ ቀበሩት። ያ ሁሉ ትውልድ ወደ አባቶቹ ከተከማቸ በኋላ እግዚአብሔርንም ሆነ እርሱ ለእስራኤል ሕዝብ ያደረገውን ነገር የማያውቅ ሌላ ትውልድ ተነሣ። ከዚያም እስራኤላውያን በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረጉ፤ የበኣል አማልክትንም አመለኩ። ከግብጽ ምድር ያወጣቸውን የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ተዉ፤ በዙሪያቸው ያሉት ሕዝቦች የሚያመልኳቸውን አማልክት ተከተሉ፤ ሰገዱላቸውም። እግዚአብሔርንም አስቈጡት፤ እግዚአብሔርንም ትተው በኣልንና አስታሮትን አምልከዋልና እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ በመቈጣቱ ለሚዘርፏቸው አሳልፎ ሰጣቸው፤ በዙሪያቸው ላሉ ጠላቶቻቸው ሸጣቸው። እስራኤላውያን ለውጊያ በሚወጡበት ጊዜ ሁሉ እግዚአብሔር አስቀድሞ በእነርሱ ላይ እንደ ተናገረውና እንደ ማለው ይሸነፉ ዘንድ የእግዚአብሔር እጅ ትከፋባቸው ነበር፤ ከዚህም የተነሣ እጅግ ተጨነቁ። እግዚአብሔርም ከእነዚህ ወራሪዎች የሚያድኗቸውን መሳፍንት አስነሣ፤ እስራኤላውያን ግን ሌሎችን አማልክት ተከትለው አመነዘሩ፤ ሰገዱላቸውም እንጂ መሳፍንታቸውን አልሰሙም። አባቶቻቸው እግዚአብሔርን በመታዘዝ በሄዱበት መንገድ ሳይሆን፣ አባቶቻቸው የእግዚአብሔርን ሕግ በመከተል ከሄዱበት መንገድ ፈጥነው ፈቀቅ አሉ። እግዚአብሔር መሳፍንትን ባሰነሣላቸው ቍጥር ከመስፍኑ ጋራ ስለሚሆን፣ እርሱ በሕይወት እስካለ ድረስ እግዚአብሔር ከጠላቶቻቸው ያድናቸው ነበር፤ ከጠላቶቻቸው ሥቃይና መከራ ሲደርስባቸው በሚጮኹበት ጊዜ እግዚአብሔር ይራራላቸው ነበር። መስፍኑ ከሞተ በኋላ ግን ሕዝቡ ሌሎችን አማልክት በመከተል፣ እነርሱን በማገልገልና በማምለክ ከአባቶቻቸው ይልቅ ወደ ክፉ መንገድ ተመለሱ፤ ክፉ ሥራቸውንና የእልኸኝነት መንገዳቸውንም አይተውም ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ እጅግ ተቈጣ፤ እንዲህም አለ፤ “ይህ ሕዝብ ለቀደሙ አባቶቹ የሰጠሁትን ቃል ኪዳን ስለ ተላለፈ፣ እኔንም ስላልሰማ፣ ኢያሱ በሞተ ጊዜ ከተዋቸው በምድሪቱ ከነበሩት ሕዝቦች አንዳቸውንም እንኳ በፊታቸው አሳድጄ አላስወጣም። ይህን የማደርገውም አባቶቻቸው እንዳደረጉት ሁሉ፣ እስራኤላውያን የእግዚአብሔርን መንገድ የሚጠብቁ መሆን አለመሆናቸውን ለማወቅ እፈትናቸው ዘንድ እነርሱን መሣሪያ ለማድረግ ነው።” ስለዚህ እግዚአብሔር እነዚያን ሕዝቦች በዚያው እንዲኖሩ አደረገ፤ በኢያሱ እጅ አሳልፎ በመስጠት ወዲያውኑ አሳድዶ አላስወጣቸውም።