አንድ ቀን ሶምሶን የፍልስጥኤማውያን ከተማ ወደሆነችው ወደ ጋዛ ሄደ፤ እዚያም አንዲት አመንዝራ ሴት አይቶ ከእርስዋ ጋር ለማደር ወደ ቤትዋ ገባ፤ የጋዛም ሰዎች ሶምሶን በዚያ መኖሩን ሰምተው ያንን ቦታ በመክበብ በከተማይቱ በር ሌሊቱን ሙሉ ሲጠብቁት ዐደሩ፤ “እስኪነጋ ጠብቀን እንገድለዋለን” ብለው በማሰብ ሌሊቱን ሙሉ አደፈጡ፤ ነገር ግን ሶምሶን ከሴቲቱ ጋር ተኝቶ የቈየው እስከ እኩለ ሌሊት ብቻ ነበር፤ ከዚያን በኋላ ከመኝታው ተነሣ፤ የከተማይቱን ቅጽር በር፥ ሁለቱን ምሶሶዎችና መቈለፊያዎቹን ሁሉ ፈነቃቀለ፤ ያንን ሁሉ በትከሻው ተሸክሞ ከኬብሮን ፊት ለፊት እስካለው ኮረብታ ድረስ ወሰደ። ከዚህ በኋላ ሶምሶን በሶሬቅ ሸለቆ የምትኖር ደሊላ ተብላ የምትጠራ አንዲት ሴት ወደደ፤ የፍልስጥኤማውያን ገዢዎች ወደ እርስዋ ሄደው እንዲህ አሉአት፤ “ሶምሶንን አግባብተሽ ይህን ሁሉ ብርታት ያገኘው ከምን እንደ ሆነና እንዴትስ አስረን በቊጥጥራችን ሥር በማድረግ ልናሸንፈው እንደምንችል ጠይቂው፤ እያንዳንዳችንም አንድ ሺህ አንድ መቶ ጥሬ ብር እንሰጥሻለን።” ስለዚህ ደሊላ ሶምሶንን “ይህን ያኽል ብርቱ የሚያደርግህ ምን እንደ ሆነ እባክህ ንገረኝ፤ አንድ ሰው አንተን አስሮ ሊያደክምህ የሚችለው እንዴት ነው?” አለችው። ሶምሶንም “እርጥብ በሆኑ ሰባት አዳዲስ ጠፍሮች ቢያስሩኝ እንደ ማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት። ከዚህ በኋላ የፍልስጥኤማውያን ገዢዎች እርጥብ የሆኑ ሰባት አዳዲስ ጠፍሮችን ለደሊላ ይዘውላት መጡ፤ እርስዋም በእርሱ ሶምሶንን አሰረችው። በሌላ ክፍል ሆነው የሚጠባበቁ ወንዶች ስለ ነበሩ እርሷ “ሶምሶን! ፍልስጥኤማውያን መጡብህ!” ስትል ጮኸች፤ እርሱ ግን ፈትል እሳት ሲነካው እንደሚበጣጠስ ጠፍሮቹን በጣጠሳቸው፤ ስለዚህ አሁንም ብርታት የሚያገኝበትን ምሥጢር ገና አልደረሱበትም ነበር። ደሊላም ሶምሶንን “እነሆ! አታለልከኝ፤ እውነቱንም አልነገርከኝም፤ አሁንም አንተን እንዴት ማሰር እንደሚቻል እባክህ ንገረኝ!” አለችው። እርሱም “ሥራ ባልተሠራበት አዲስ ገመድ ቢያስሩኝ እንደማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” ሲል መለሰላት። ደሊላም አዲስ ገመድ ወስዳ አሰረችው፤ በሌላ ክፍል ሆነው የሚጠባበቁ ወንዶች ስለ ነበሩ እርሷ “ሶምሶን፥ ፍልስጥኤማውያን መጡብህ” ስትል ጮኸች፤ እርሱ ግን ገመዱን ከክንዱ እንደ ፈትል በጣጠሰው። ደሊላም ሶምሶንን “እስከ አሁን ድረስ አሞኘኸኝ፤ እውነቱንም አልነገርከኝም፤ አሁንም አንተን እንዴት ማሰር እንደሚቻል እባክህ ንገረኝ” አለችው። እርሱም “የራሴን ጠጒር ሰባቱን ቁንዳላዎች ከድር ጋር ብትጐነጒኚው፥ በችካልም ብትቸክዪው እንደማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት። ከዚህ በኋላ ደሊላ ተኝቶ ሳለ የራሱን ጠጒር ሰባቱን ቁንዳላዎች ከድር ጋር ጐንጒና በችካል ቸከለችው፤ ከዚያ በኋላ “ሶምሶን! ፍልስጥኤማውያን መጡብህ!” ብላ ጮኸች፤ እርሱ ግን ከእንቅልፉ ነቅቶ ጠጒሩን ከችካሉና ከድሩ ላይ ነቀለው። ስለዚህ እርስዋ “ልብህ ከእኔ ጋር ሳይሆን እንዴት እወድሻለሁ ትለኛለህ? ሦስት ጊዜ አታለልከኝ፤ እስከ አሁንም ይህን ሁሉ ብርታት ያገኘኸው ከምን እንደ ሆነ አልነገርከኝም” አለችው። ዕለት ዕለትም እየነዘነዘች ሞቱን እስከሚመኝ ድረስ አስጨነቀችው፤ በመጨረሻ እውነቱን ነገራት፤ እንዲህም አላት፦ “ከተወለድኩበት ጊዜ ጀምሮ በናዝራዊነት ለእግዚአብሔር የተለየሁ ስለ ሆነ ጠጒሬ ተላጭቶ አያውቅም፤ ጠጒሬ ቢላጭ ግን ኀይል ተለይቶኝ እንደማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ።”
መጽሐፈ መሳፍንት 16 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ መሳፍንት 16:1-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos