አንድ ቀን ሳምሶን ወደ ጋዛ ሄደ፤ እዚያም አንዲት ዝሙት ዐዳሪ አየ፤ አብሯት ለማደርም ገባ። የጋዛ ሰዎች፣ “ሳምሶን እዚህ ነው!” የሚል ወሬ ደረሳቸው፤ ስለዚህም ሰዎቹ ቦታውን ከብበው፤ ሌሊቱን በሙሉ በከተማዪቱ ቅጥር በር ላይ አድፍጠው ጠበቁት፤ “በማለዳ እንገድለዋለን” በማለትም ሌሊቱን በሙሉ እንዳደፈጡ ዐደሩ። ነገር ግን ሳምሶን እዚያ የተኛው እስከ እኩለ ሌሊት ብቻ ነበር፤ ተነሥቶም የከተማዪቱን ቅጥር በር ከሁለት መቃኖቹ ጋር መወርወሪያውንና ማያያዣውን ጭምር በሙሉ ነቅሎ በትከሻው ላይ ካደረገ በኋላ፣ በኬብሮን ፊት ለፊት እስካለው ኰረብታ ጫፍ ድረስ ተሸክሞት ወጣ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሳምሶን በሶሬቅ ሸለቆ የምትኖር ደሊላ የምትባል አንዲት ሴት ወደደ። የፍልስጥኤማውያን ገዦች ወደ እርሷ ሄደው፣ “እርሱን አስረን በቍጥጥራችን ሥር በማዋል ልናሸንፈው እንዴት እንደምንችልና የብርታቱ ታላቅነት ምስጢር ምን እንደ ሆነ እንዲያሳይሽ እስቲ አባብዪው፤ ይህን ካደረግሽ እያንዳንዳችን አንድ ሺሕ አንድ መቶ ሰቅል ጥሬ ብር እንሰጥሻለን” አሏት። ስለዚህም ደሊላ ሳምሶንን፣ “የብርታትህን ታላቅነት ምስጢርና ታስረህ በቍጥጥር ሥር የምትውለው እንዴት እንደ ሆነ እባክህ ንገረኝ” አለችው። ሳምሶንም፣ “ማንም ባልደረቁ ሰባት እርጥብ ጠፍሮች ቢያስረኝ እንደ ማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት። ከዚያም የፍልስጥኤማውያን ገዦች ያልደረቁ ሰባት እርጥብ ጠፍሮች አመጡላት፤ እርሷም አሰረችው። ሰዎች በጓዳ ውስጥ ተደብቀው ነበር፤ እርሷም፣ “ሳምሶን ፍልስጥኤማውያን መጡብህ” አለችው፤ ሳምሶን ግን ፈትል እሳት ሲነካው እንደሚበጣጠስ ጠፍሮቹን በቀላሉ በጣጠሳቸው። ስለዚህ የብርታቱ ምስጢር ምን እንደ ሆነ ሊታወቅ አልቻለም። ደሊላም ሳምሶንን፣ “አሞኝተኸኛል፤ ዋሽተኸኛል፤ እባክህ አሁንም አንተን እንዴት ማሰር እንደሚቻል ንገረኝ” አለችው። እርሱም፣ “ሥራ ላይ ባልዋሉ አዳዲስ ገመዶች ቢያስሩኝ እንደ ማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት። ደሊላም አዳዲስ ገመዶች ወስዳ አሰረችው፤ ሰዎች በጓዳ ውስጥ ተደብቀው ነበር፤ እርሷም፣ “ሳምሶን ፍልስጥኤማውያን መጡብህ” አለችው። እርሱ ግን ክንዱ የታሰረባቸውን ገመዶች እንደ ፈትል ክር በጣጠሳቸው። ደግሞም ደሊላ ሳምሶንን፣ “እስካሁን አሞኝተኸኛል፤ ዋሽተኸኛል። እባክህን አንተን ማሰር የሚቻለው እንዴት እንደ ሆነ ንገረኝ” አለችው። እርሱም መልሶ፣ “የራስ ጠጕሬን ሰባት ቈንዳላዎች ከድር ጋር ጐንጕነሽ በችካል ብትቸክዪው፣ እንደ ማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት። ደሊላም መተኛቱን አይታ ሰባቱን ቈንዳላዎቹን ከድር ጋር ጐነጐነችው፤ ከችካልም ጋር ቸከለችው። እንደ ገናም፣ “ሳምሶን! ፍልስጥኤማውያን መጡብህ” አለችው። ሳምሶን ከእንቅልፉ ነቃ፤ ችካሉን ከነድሩ፣ ከነቈንዳላው ነቀለው። ከዚያም፣ “ሳታምነኝ እንዴት ‘እወድሻለሁ’ ትለኛለህ? ስታታልለኝና የኀይልህንም ታላቅነት ምስጢር ስትደብቀኝ ይህ ሦስተኛ ጊዜህ ነው” አለችው። በሕይወት መኖሩን እስኪጠላ ድረስ ዕለት ዕለት በመጨቅጨቅ አሰለቸችው። ስለዚህ ሁሉንም ነገር ነገራት፤ እንዲህም አለ፤ “ከተወለድሁ ጀምሮ ናዝራዊ በመሆን ለእግዚአብሔር የተለየሁ ስለሆንሁ ራሴን ምላጭ ነክቶት አያውቅም፤ የራሴ ጠጕር ቢላጭ ግን ኀይሌ ተለይቶኝ እንደ ማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት።
መሳፍንት 16 ያንብቡ
ያዳምጡ መሳፍንት 16
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መሳፍንት 16:1-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos