የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የያዕቆብ መልእክት 5:7-20

የያዕቆብ መልእክት 5:7-20 አማ05

ወንድሞች ሆይ! እንግዲህ ጌታ እስኪመጣ ድረስ በትዕግሥት ጠብቁ፤ ገበሬ መሬቱ የመጀመሪያውንና የኋለኛውን ዝናብ እስከሚያገኝ እየታገሠ ክቡር ዋጋ ያለውን የመሬቱን ፍሬ ይጠባበቃል። እናንተም እንዲሁ ታገሡ፤ የጌታ መምጫ ጊዜ ስለ ተቃረበ በተስፋ ጽኑ። ወንድሞች ሆይ! በእናንተም ላይ እንዳይፈረድባችሁ እርስ በርሳችሁ አትጨቃጨቁ፤ እነሆ ፈራጁ የሚመጣበት ጊዜ ደርሶአል። ወንድሞች ሆይ፥ በጌታ ስም የተናገሩት ነቢያት መከራን በትዕግሥት በመቀበል ምሳሌ መሆናቸውን ዕወቁ። ደግሞም እነዚያን በትዕግሥት የጸኑትን “የተባረኩ ናቸው” እንላቸዋለን፤ ኢዮብ እንዴት እንደ ታገሠ ሰምታችኋል። ጌታም በመጨረሻ ያደረገለትን መልካም ነገር አይታችኋል፤ በዚህም ጌታ መሐሪና ርኅሩኅ መሆኑን ተመልክታችኋል። ወንድሞቼ ሆይ! ከሁሉም በላይ በሰማይ ወይም በምድር ወይም በሌላ በምንም ነገር አትማሉ፤ ንግግራችሁ አዎ ከሆነ በእውነት አዎ ይሁን፤ አይደለም ከሆነም በእውነት አይደለም ይሁን፤ እንዲህ ካልሆነ ግን ይፈረድባችኋል። ከእናንተ መካከል ችግር የደረሰበት ሰው ቢኖር ይጸልይ፤ ደስ ያለው ሰውም ቢኖር እግዚአብሔርን በማመስገን ይዘምር። ከእናንተ መካከል የታመመ ሰው ቢኖር የቤተ ክርስቲያን ካህናትን (ሽማግሌዎችን) ወደ እርሱ ይጥራ፤ እነርሱም በሽተኛውን በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። እንዲህ ዐይነቱ በእምነት ላይ የተመሠረተ ጸሎት በሽተኛውን ያድነዋል፤ ጌታም ከበሽታው ይፈውሰዋል፤ የሠራው ኃጢአትም ቢኖር ይቅር ይባልለታል። ስለዚህ እንድትፈወሱ ኃጢአታችሁን እርስ በርሳችሁ ተናዘዙ፤ እያንዳንዱም ለሌላው ይጸልይ፤ የጻድቅ ሰው ጸሎት ብዙ ውጤት የሚያስገኝ ታላቅ ኀይል አለው፤ ኤልያስ እንደ እኛ ሰው ነበረ፤ ነገር ግን ዝናብ እንዳይዘንብ አጥብቆ በጸለየ ጊዜ ለሦስት ዓመት ተኩል በምድር ላይ ምንም ዝናብ አልዘነበም። እንደገና በጸለየም ጊዜ ሰማይ ዝናብ ሰጠ፤ ምድርም እንደገና ፍሬን ሰጠች። ወንድሞቼ ሆይ! ከእናንተ አንዱ ከእውነት መንገድ ቢወጣና ሌላው ወደ እውነት መንገድ ቢመልሰው ኃጢአተኛውን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልስ፥ የኃጢአተኛውን ነፍስ ከሞት እንደሚያድንና የብዙ ኃጢአቱንም ይቅርታ እንደሚያስገኝለት ይወቅ።