እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ጌታ እስከሚመጣ ድረስ ታገሡ። ገበሬ መሬቱ መልካምን ፍሬ እስከሚሰጥ ድረስ እንዴት እንደሚታገሥ፣ የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እንዴት እንደሚጠባበቅ አስተውሉ። እናንተም እንዲሁ ታገሡ፤ ልባችሁንም አጽኑ፤ ምክንያቱም የጌታ መምጫ ተቃርቧል። ወንድሞች ሆይ፤ እርስ በርሳችሁ አታጕረምርሙ፤ አለዚያ ይፈረድባችኋል፤ እነሆ፤ ፈራጁ በበር ላይ ቆሟል። ወንድሞች ሆይ፤ በጌታ ስም የተናገሩትን ነቢያት የመከራና የትዕግሥት ምሳሌ አድርጋችሁ ተመልከቱ። በትዕግሥት የጸኑትን የተባረኩ አድርገን እንደምንቈጥር ታውቃላችሁ፤ ኢዮብ እንዴት ታግሦ እንደ ጸና ሰምታችኋል፤ ጌታም በመጨረሻ ያደረገለትን አይታችኋል። ጌታ እጅግ ርኅሩኅና መሓሪ ነው። ከሁሉም በላይ ወንድሞቼ ሆይ፤ በሰማይ ወይም በምድር ወይም በማናቸውም ነገር ቢሆን አትማሉ፤ “አዎ” ቢሆን አዎ ይሁን፤ “አይደለም” ቢሆን አይደለም ይሁን፤ አለዚያ ይፈረድባችኋል። ከእናንተ መካከል በመከራ ውስጥ ያለ አለ? እርሱ ይጸልይ፤ የተደሰተ አለ? የምስጋና መዝሙር ይዘምር። ከእናንተ መካከል የታመመ ሰው አለ? የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን ይጥራ፤ እነርሱም በጌታ ስም ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። በእምነት የቀረበ ጸሎት የታመመውን ሰው ይፈውሰዋል፤ ጌታም ያስነሣዋል፤ ኀጢአትም ሠርቶ ከሆነ፣ ይቅር ይባላል። ስለዚህ ኀጢአታችሁን እርስ በርሳችሁ ተናዘዙ፤ ትፈወሱም ዘንድ አንዱ ለሌላው ይጸልይ። የጻድቅ ሰው ጸሎት ኀይል አለው፤ ታላቅ ነገርም ያደርጋል። ኤልያስ እንደ እኛ ሰው ነበረ፤ ዝናብ እንዳይዘንብ አጥብቆ ጸለየ፤ በምድርም ላይ ሦስት ዓመት ተኩል ዝናብ አልዘነበም። እንደ ገናም ጸለየ፤ ዝናብም ከሰማይ ዘነበ፤ ምድርም ፍሬዋን ሰጠች። ወንድሞቼ ሆይ፤ ከእናንተ አንዱ ከእውነት ቢስትና ሌላው ቢመልሰው፣ ይህን አስተውሉ፤ ኀጢአተኛን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልስ ሰው ነፍሱን ከሞት ያድነዋል፤ ብዙ ኀጢአትንም ይሸፍናል።
ያዕቆብ 5 ያንብቡ
ያዳምጡ ያዕቆብ 5
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ያዕቆብ 5:7-20
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos