ትንቢተ ኢሳይያስ 63
63
የእግዚአብሔር ድልና የማዳን ኀይሉ
1ከኤዶም ቦጽራ ቀይ መጐናጸፊያ ተጐናጽፎ የሚመጣው ይህ ማነው? በታላቅ ኀይሉ አስደናቂ ልብስ ለብሶ የሚራመደው ይህ ማነው? “ፍርድን የምሰጥ የማዳን ኀይል ያለኝ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”
2“የወይን ጠጅ ጨምቆ ለማውጣት የወይን ፍሬ ሲጨምቅ እንደ ነበረ ሰው ልብስህ ስለምን ቀይ ሆነ?”
3እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ይመልሳል “እኔ ብቻዬን አሕዛብን ሁሉ እንደ ወይን ረገጥኩ፤ ይህን በማደርግበት ጊዜ ከሕዝቦች ከእኔ ጋር ማንም አልነበረም፤ እኔ በቊጣዬ ረገጥኳቸው፤ በመዓቴም አደቀቅኋቸው፤ ደማቸውም በልብሴ ላይ ተረጨ። #ራዕ. 14፥20፤ 19፥13፤15። 4የምበቀልበትን ጊዜ ወስኜአለሁ፤ ሕዝቤን የምታደግበትም ጊዜ ደርሶአል። 5ዙሪያዬን በተመለከትኩ ጊዜ የሚረዳ ማንም አልነበረም። ደጋፊ ባለመኖሩ ተደነቅሁ፤ ስለዚህ በኀይለኛ ቊጣዬ አማካይነት እኔው ራሴ ድልን አመጣሁ። #ኢሳ. 59፥16። 6ሰዎችን በቊጣዬ ረግጬ ጣልኳቸው፤ ኀይለኛ ቊጣዬ እንዲሰማቸው አደረግሁ፤ ደማቸውንም በምድር ላይ አፈሰስኩ።”
እግዚአብሔር ለእስራኤል ያሳየው ቸርነት
7ለእኛ ስላደረጋቸው ድርጊቶች ሁሉ፥
ለእስራኤል ሕዝብ እንደ መሐሪነቱ ስላሳየው ከፍተኛ በጎ አመለካከት፥ ስለ ተትረፈረፈውም ዘለዓለማዊ ፍቅሩ የእግዚአብሔርን ቸርነት ምስጉን ድርጊቶቹን እዘረዝራለሁ።
8እግዚአብሔር “በእርግጥ እነርሱ የእኔ ወገኖችና የማይዋሹ ልጆች ናቸው” አለ። ለእነርሱም አዳኛቸው ሆነ። 9በችግራቸው ጊዜ ሁሉ ያዳናቸው በመልእክተኛ ወይም በመልአክ አማካይነት ሳይሆን እርሱ በመካከላቸው በመገኘት ነው፤ በፍቅሩና በርኅራኄውም ታደጋቸው፤ እርሱም በቀድሞ ዘመናት ሁሉ አንሥቶ ልጁን እንደሚሸከም ሰው ተንከባከባቸው። 10ሆኖም እነርሱ የእርሱን ቅዱስ መንፈስ አሳዘኑ፤ ስለዚህ እሱ በእነርሱ ላይ ተነሥቶ ቀጣቸው።
11ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ የነበረበትን የቀድሞውን ዘመን ማስታወስ ጀመሩ፤ ከመንጋዎቹ እረኞች ጋር ከባሕር ያወጣቸው እግዚአብሔር የት አለ? ቅዱስ መንፈሱን በውስጣቸው ያሳደረው እግዚአብሔር የት ነው? 12ለራሱ ዘለዓለማዊ ስም ይሆን ዘንድ በፊታቸው ውሃን ለመክፈል ክብርን የተመላ ኀይሉን በሙሴ ቀኝ በኩል እንዲራመድ ያደረገው የት አለ? #ዘፀ. 14፥21። 13በጥልቁ ሲሄዱ እንዳይሰናከሉ ለጥ ባለ ሜዳ ላይ እንዳለ ፈረስ አደረጋቸው። 14እንዲሁም በሸለቆው ውስጥ እንደሚሄድ የከብት መንጋ የእግዚአብሔር መንፈስ ዕረፍትን ሰጣቸው። ስምህ ይከብር ዘንድ ሕዝብህን በዚህ ዐይነት መራሃቸው።
ምሕረትንና ርዳታን ለማግኘት የቀረበ ጸሎት
15እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! ከተቀደሰውና ከክቡር መኖሪያህ ከሰማይ ወደ ታች ተመልከት፤ ቅንአትህና ኀይልህ የት አሉ? መልካም ፈቃድህና ርኅራኄህስ የት አለ? እነርሱ ከእኛ ርቀዋል። 16አብርሃም ባያውቀን፥ እስራኤል ባይቀበለንም እንኳ አንተ አባታችን ነህ፤ አምላክ ሆይ! ስምህ ከጥንት እንደ ሆነ ሁሉ አንተ አባታችን ነህ፤ አንተ ታዳጊአችን ነህ። 17አምላክ ሆይ! ለምን መንገድህን እንድንስት አደረግኸን? እንዳንፈራህስ ለምን ልባችንን አደነደንክ? ለአገልጋዮችህ፥ የአንተ ስለ ሆኑት ነገዶች ስትል እባክህ ተመለስ።
18ለጥቂት ጊዜ ቤተ መቅደስህ የቅዱስ ሕዝብህ ንብረት ነበር፤ አሁን ግን ጠላቶቻችን ረገጡት። 19እኛ በአንተ እንዳልተገዙና በስምህ እንዳልተጠሩ ወገኖች ከሆንን ብዙ ጊዜአችን ነው።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 63: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997