ትንቢተ ኢሳይያስ 62
62
1የሚሰጣት ፍርድ እንደ ንጋት እስኪፈነጥቅና
መዳንዋም እንደሚነድ ችቦ እስኪበራ ድረስ፥
ስለ ጽዮን ዝም አልልም፤
ስለ ኢየሩሳሌምም ከማሰብ አላርፍም።
2ሕዝቦች የሚሰጥሽን ፍርድ፥ ነገሥታትም ክብርሽን ያያሉ፤
አንቺም እግዚአብሔር በሚያወጣልሽ አዲስ ስም ትጠሪአለሽ።
3አንቺ በእግዚአብሔር እጅ እንዳለው የተዋበ አክሊልና
በአምላክሽም እጅ እንዳለው የነገሥታት ዘውድ ትሆኚአለሽ።
4ከእንግዲህ ወዲህ “የተተወች” ተብለሽ አትጠሪም፤
ምድርሽም “ባድማ” ተብላ አትጠራም።
የምትጠሪበትም አዲስ ስም፥
“እግዚአብሔር በእርስዋ ደስ ይለዋል!” የሚል ይሆናል፤
ምድርሽም “ባለ ባል” ተብላ ትጠራለች፤
እግዚአብሔር በአንቺ ደስ ይለዋል፤
ምድርሽም ባል እንዳላት ሴት ትሆናለች።
5ጐልማሳ ድንግሊቱን ሙሽራ አድርጎ እንደሚወስድ፥
የፈጠረሽ እግዚአብሔርም ለአንቺ እንደ ባል ይሆንልሻል፤
ወንዱም ሙሽራ በሴትዋ ሙሽራ ደስ እንደሚሰኝ፥
እግዚአብሔርም በአንቺ ደስ ይለዋል።
6ኢየሩሳሌም ሆይ! በቅጥሮችሽ ላይ ቀንና ሌሊት ዝም የማይሉ
ጠባቂዎችን አኑሬአለሁ፤
እናንተ እግዚአብሔርን የምትለምኑ
ዕረፍት አታድርጉ።
7ኢየሩሳሌምን እስኪመሠርታትና
በምድር ሁሉ ዝነኛ ከተማ እስከሚያደርጋት ድረስ ሳታቋርጡ አሳስቡት።
8እግዚአብሔር በኃይሉና በሥልጣኑ እንዲህ ሲል ማለ፦
“ከእንግዲህ ወዲያ እህልሽን ጠላቶችሽ እንዲበሉት አላደርግም፤
የደከምሽበትን አዲስ የወይን ጠጅሽንም ባዕዳን እንዲጠጡት አላደርግም።
9ነገር ግን በጐተራ የሰበሰቡትን እህል እነርሱ ራሳቸው በልተው
እኔ እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ፤
የሰበሰቡትንም የወይን ዘለላ የወይን ጠጅ እነርሱ ራሳቸው
በተቀደሰ አደባባዬ ይጠጡታል።
10በቅጥር በሩ በኩል ዕለፉ፤
ለሰዎች መንገዱን አዘጋጁ፤
አውራ ጐዳናውን ሥሩ፤
ድንጋዮችን አስወግዱ፤
አርማውንም ለሕዝቦች ከፍ አድርጉ።”
11እግዚአብሔር ለዓለም ሁሉ እንዲህ ብሎ ያውጃል፦
“አዳኝሽ ይመጣል፤ ከእርሱም ጋር ለሰዎች የሚከፍለው
ዋጋና ሽልማት አለ ብላችሁ ለጽዮን ልጅ ንገሩአት።”
12ሕዝቡ “የተቀደሱና እግዚአብሔር የታደጋቸው ወገኖች”
ተብለው ይጠራሉ፤
አንቺም ኢየሩሳሌም “የተፈለገችና
ያልተተወች ከተማ” ተብለሽ ትጠሪአለሽ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 62: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997