የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 61

61
ደኅንነትን የሚያበሥር መልካም ዜና
1ለተጨቈኑት መልካም ዜናን አበሥር ዘንድ፥
ልባቸው የተሰበረውን እጠግን ዘንድ፥
ለተማረኩት ነጻነትን፥ ለታሰሩት መፈታትን
ለማወጅ እግዚአብሔር ቀብቶ ስለ ላከኝ፥
የጌታ እግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው። #ማቴ. 11፥5፤ ሉቃ. 7፥22።
2የእግዚአብሔርን የምሕረት ዓመትና
የአምላካችንን የበቀል ቀን እንዳውጅ፥
የሚያለቅሱትን ሁሉ እንዳጽናና፥ #ሉቃ. 4፥18-19።
3በጽዮን ለሚያለቅሱት ሰዎች
በዐመድ ፈንታ የአበባ ጒንጒንን፥
በእንባቸው ምትክ የወይራ ዘይትን
በኀዘን ፈንታ የደስታ ዘይትን፥
በዛለ መንፈሳቸው ፈንታ የምስጋና መጐናጸፊያን
ለማስገኘት ላከኝ።
እነርሱም ክብሩን እንዲገልጡ እግዚአብሔር የተከላቸው
“የጽድቅ ዋርካዎች” ተብለው ይጠራሉ።
4እነርሱ የጥንት ፍርስራሾችን ይገነባሉ፤
ቀደም ብለው የወደሙትን እንደገና ይሠራሉ፤
በየትውልዱ የፈራረሱትን ከተሞች ያድሳሉ፤
5የባዕድ አገር ሕዝቦች መንጋዎቻችሁን ያሰማራሉ፤
ምድራችሁን ያርሳሉ፤
የወይን ተክሎቻችሁንም ይንከባከባሉ።
6እናንተ ግን “የእግዚአብሔር ካህናትና
የአምላካችን አገልጋዮች” ተብላችሁ ትጠራላችሁ።
በሕዝቦች ሀብት ትደሰታላችሁ፤
በብልጽግናቸውም ትከብራላችሁ።
7ኀፍረታቸው እጥፍ ስለ ነበረ፤
ውርደትም የእነርሱ ዕድል ፈንታ መሆኑ ስለ ታወጀ
ስለዚህ ድርሻቸው እጥፍ ይሆናል፤
ዘለዓለማዊ ደስታም ያገኛሉ።
8እኔ እግዚአብሔር ፍትሕን እወዳለሁ፤
ቅሚያንና ክፉ ድርጊትን እጠላለሁ፤
እኔ ተገቢ ዋጋቸውን እሰጣቸዋለሁ፤
ከእነርሱም ጋር ዘለዓለማዊ ቃል ኪዳን እገባለሁ።
9ልጆቻቸው በወገኖች ዘንድ፥ የልጅ ልጆቻቸውም በሕዝቦች ዘንድ
የታወቁ ይሆናሉ።
የሚያዩአቸው ሁሉ በእኔ በእግዚአብሔር የተባረኩ ዘሮች መሆናቸውን ያውቃሉ።
10እኔ በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤
ሁለንተናዬም በአምላኬ ሐሴትን ያደርጋል፤
የአበባ አክሊል በራሱ ላይ እንደሚያደርግ ሙሽራ፥
በጌጣጌጥም እንዳሸበረቀች ሙሽሪት አድርጎ፥
የመዳንን ልብስ አልብሶኛል፤
የጽድቅንም መጐናጸፊያ ደርቦልኛል። #ራዕ. 21፥2።
11ምድር ቡቃያዎችን እንደምታበቅል፥
የአትክልት ቦታም ተክሎችን እንደምታሳድግ፥
ጌታ እግዚአብሔርም ጽድቅና ምስጋና
ከሕዝቦች ሁሉ ዘንድ እንዲፈልቁ ያደርጋል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ