ለተጨቈኑት መልካም ዜናን አበሥር ዘንድ፥ ልባቸው የተሰበረውን እጠግን ዘንድ፥ ለተማረኩት ነጻነትን፥ ለታሰሩት መፈታትን ለማወጅ እግዚአብሔር ቀብቶ ስለ ላከኝ፥ የጌታ እግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው። የእግዚአብሔርን የምሕረት ዓመትና የአምላካችንን የበቀል ቀን እንዳውጅ፥ የሚያለቅሱትን ሁሉ እንዳጽናና፥ በጽዮን ለሚያለቅሱት ሰዎች በዐመድ ፈንታ የአበባ ጒንጒንን፥ በእንባቸው ምትክ የወይራ ዘይትን በኀዘን ፈንታ የደስታ ዘይትን፥ በዛለ መንፈሳቸው ፈንታ የምስጋና መጐናጸፊያን ለማስገኘት ላከኝ። እነርሱም ክብሩን እንዲገልጡ እግዚአብሔር የተከላቸው “የጽድቅ ዋርካዎች” ተብለው ይጠራሉ። እነርሱ የጥንት ፍርስራሾችን ይገነባሉ፤ ቀደም ብለው የወደሙትን እንደገና ይሠራሉ፤ በየትውልዱ የፈራረሱትን ከተሞች ያድሳሉ፤ የባዕድ አገር ሕዝቦች መንጋዎቻችሁን ያሰማራሉ፤ ምድራችሁን ያርሳሉ፤ የወይን ተክሎቻችሁንም ይንከባከባሉ። እናንተ ግን “የእግዚአብሔር ካህናትና የአምላካችን አገልጋዮች” ተብላችሁ ትጠራላችሁ። በሕዝቦች ሀብት ትደሰታላችሁ፤ በብልጽግናቸውም ትከብራላችሁ። ኀፍረታቸው እጥፍ ስለ ነበረ፤ ውርደትም የእነርሱ ዕድል ፈንታ መሆኑ ስለ ታወጀ ስለዚህ ድርሻቸው እጥፍ ይሆናል፤ ዘለዓለማዊ ደስታም ያገኛሉ። እኔ እግዚአብሔር ፍትሕን እወዳለሁ፤ ቅሚያንና ክፉ ድርጊትን እጠላለሁ፤ እኔ ተገቢ ዋጋቸውን እሰጣቸዋለሁ፤ ከእነርሱም ጋር ዘለዓለማዊ ቃል ኪዳን እገባለሁ። ልጆቻቸው በወገኖች ዘንድ፥ የልጅ ልጆቻቸውም በሕዝቦች ዘንድ የታወቁ ይሆናሉ። የሚያዩአቸው ሁሉ በእኔ በእግዚአብሔር የተባረኩ ዘሮች መሆናቸውን ያውቃሉ። እኔ በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤ ሁለንተናዬም በአምላኬ ሐሴትን ያደርጋል፤ የአበባ አክሊል በራሱ ላይ እንደሚያደርግ ሙሽራ፥ በጌጣጌጥም እንዳሸበረቀች ሙሽሪት አድርጎ፥ የመዳንን ልብስ አልብሶኛል፤ የጽድቅንም መጐናጸፊያ ደርቦልኛል።
ትንቢተ ኢሳይያስ 61 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ኢሳይያስ 61:1-10
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች