የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 59:1-21

ትንቢተ ኢሳይያስ 59:1-21 አማ05

እግዚአብሔር ሰውን ማዳንና ጸሎትን መስማት የሚሳነው አይደለም። በደላችሁ በእናንተና በእግዚአብሔር መካከል ሆኖ ጋረደ፤ ኃጢአታችሁ ከእግዚአብሔር ስለ ለያችሁ ጸሎታችሁ አይሰማም። እጆቻችሁ በደም፥ ጣቶቻችሁም በበደል ተበክለዋል፤ አፋችሁ ውሸትን ይናገራል፤ በአንደበቶቻችሁም ታጒተመትማላችሁ። ማንም ሰው ክስ ሲመሠርት ትክክለኛውን ጉዳይ ይዞ አይመጣም ወደ ፍርድ ሸንጎም ሲቀርብ ለሕግ ታማኝ ሆኖ አይደለም፤ እነርሱ ከንቱ በሆነ አቤቱታ ላይ ተመሥርተው ውሸትን ይናገራሉ፤ ተንኰልን አስበው በደልን ይፈጽማሉ። እነርሱ የእባብ ዕንቊላል ይቀፈቅፋሉ፤ የሸረሪት ድርም ይፈትላሉ፤ እነዚያን ዕንቊላሎች የሚበላ ሁሉ ይሞታል፤ ከሚቀፈቀፈው ዕንቊላል እፉኝት ይወጣል። የሸረሪት ድር ልብስ ለመሥራት አይጠቅምም፤ ማንም ለልብስ አይጠቀምበትም፤ ሥራቸው የበደል ሥራ ነው፤ እጆቻቸውም በዐመፅ ሥራ የተሞሉ ናቸው። እነርሱ ወደ ክፉ ሥራ ይሮጣሉ፤ ንጹሕ ደምንም ለማፍሰስ ይቸኲላሉ፤ ሐሳባቸው የበደል ሐሳብ ነው፤ በሚያልፉበት ቦታ ሁሉ ማጥፋትና ማፈራረስ ልማዳቸው ነው፤ የሰላምን መንገድ አያውቁትም፤ ሥራቸው ሁሉ ፍትሕ የጐደለው ነው፤ ጠማማ የሆነውን አካሄድ ስለሚከተሉ በዚያ የሚያልፍ ሁሉ ሰላም አያገኝም። ሕዝቡ እንዲህ ይላሉ፦ “ፍትሕ ከእኛ ርቆአል፤ ጽድቅም ወደ እኛ አይደርስም፤ ብርሃን እንዲበራልን እንፈልጋለን፤ ነገር ግን ሁሉም ጨለማ ነው፤ ስለዚህ በድቅድቅ ጨለማ እንመላለሳለን። በዳበሳ እንሄዳለን፤ መንገዳችንንም የምንከታተለው በዳበሳ ነው፤ በድንግዝግዝታ እንዳለን ዐይነት በቀትር እንደናቀፋለን፤ በኀያላን ሰዎችም መካከል እንደ ሞቱ ሰዎች ነን። ሁላችንም እንደ ድብ በመጮኽ እንደ ርግብም ምርር ብለን በማልቅስ ፍትሕንና መዳንን ለማግኘት እንጠባበቃለን፤ እነርሱ ግን ከእኛ የራቁ ስለ ሆኑ አይገኙም። “በደላችን በአንተ ፊት ብዙ መሆኑን ኃጢአታችን በእኛ ላይ ይመሰክራል፤ ሁልጊዜ እንበድላለን፤ መበደላችንንም እናውቃለን። በእግዚአብሔር ላይ ያለንን እምነት በማጓደል ዐምፀናል፤ አምላካችንን ትተን ወደ ኋላ አፈግፍገናል፤ በልባችን ውስጥ ውሸትን አውጠንጥነን ስም በማጥፋትና በከሐዲነት ገልጠናቸዋል። በሕዝብ አደባባይ እውነት ስለ ተሰናከለና ታማኝነት ሊገባ ስላልቻለ ፍትሕ ወደ ኋላ ተመልሶአል፤ ጽድቅም ተዳክሞአል። እውነት ጠፍቶአል፤ ከክፉ ሥራ የሚመለስ የሌሎች መሳለቂያ ይሆናል፤ እግዚአብሔርም ፍትሕ አለመኖሩን አይቶ አዘነ። ተጨቋኞችን የሚረዳ አንድ ሰው እንኳ አለመገኘቱ አስገረመው፤ ስለዚህ እነርሱን ለማዳን በኀይሉ ተጠቅሞ ድልን እንዲጐናጸፉ አደረጋቸው። እርሱ ጽድቅን እንደ ደረት ጥሩር፥ ማዳንንም እንደ ራስ ቊር ይለብሳል፤ በቀልን እንደ ልብስ ይጐናጸፋል፤ ቊጣንም እንደ ካባ ይደርባል። ተቃዋሚዎቹን በመቈጣት፥ በጠላቶቹና በጠረፍ በሚኖሩት ላይ በመበቀል እንደ ተግባራቸው ይከፍላቸዋል። እርሱ በኀይለኛ ነፋስ እየተነዳ እንደሚመጣ ጐርፍ ስለ ሆነ በምዕራብ ያሉ ሕዝቦች የእግዚአብሔርን ስም በምሥራቅ ያሉት ክብሩን ይፈራሉ።” እግዚአብሔር ለሕዝቡ እንዲህ ይላል፦ “ለጽዮንና፥ ከኃጢአታቸው በንስሓ ለሚመለሱም አዳኝ ይመጣል።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ከእነርሱ ጋር የሚኖረኝ ቃል ኪዳን ይህ ነው፦ ከአሁን ጀምሮ እስከ ዘለዓለም በእናንተ ላይ ያለው መንፈሴና በአንደበታችሁ ያኖርኩትን ቃሌን ለልጆቻችሁና ለልጅ ልጆቻችሁ አስተምሩ ይላል እግዚአብሔር።”