የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 59

59
ነቢዩ የሕዝቡን ኃጢአት ማውገዙ
1እግዚአብሔር ሰውን ማዳንና ጸሎትን መስማት የሚሳነው አይደለም። 2በደላችሁ በእናንተና በእግዚአብሔር መካከል ሆኖ ጋረደ፤ ኃጢአታችሁ ከእግዚአብሔር ስለ ለያችሁ ጸሎታችሁ አይሰማም። 3እጆቻችሁ በደም፥ ጣቶቻችሁም በበደል ተበክለዋል፤ አፋችሁ ውሸትን ይናገራል፤ በአንደበቶቻችሁም ታጒተመትማላችሁ።
4ማንም ሰው ክስ ሲመሠርት ትክክለኛውን ጉዳይ ይዞ አይመጣም ወደ ፍርድ ሸንጎም ሲቀርብ ለሕግ ታማኝ ሆኖ አይደለም፤ እነርሱ ከንቱ በሆነ አቤቱታ ላይ ተመሥርተው ውሸትን ይናገራሉ፤ ተንኰልን አስበው በደልን ይፈጽማሉ። 5እነርሱ የእባብ ዕንቊላል ይቀፈቅፋሉ፤ የሸረሪት ድርም ይፈትላሉ፤ እነዚያን ዕንቊላሎች የሚበላ ሁሉ ይሞታል፤ ከሚቀፈቀፈው ዕንቊላል እፉኝት ይወጣል። 6የሸረሪት ድር ልብስ ለመሥራት አይጠቅምም፤ ማንም ለልብስ አይጠቀምበትም፤ ሥራቸው የበደል ሥራ ነው፤ እጆቻቸውም በዐመፅ ሥራ የተሞሉ ናቸው። 7እነርሱ ወደ ክፉ ሥራ ይሮጣሉ፤ ንጹሕ ደምንም ለማፍሰስ ይቸኲላሉ፤ ሐሳባቸው የበደል ሐሳብ ነው፤ በሚያልፉበት ቦታ ሁሉ ማጥፋትና ማፈራረስ ልማዳቸው ነው፤ 8የሰላምን መንገድ አያውቁትም፤ ሥራቸው ሁሉ ፍትሕ የጐደለው ነው፤ ጠማማ የሆነውን አካሄድ ስለሚከተሉ በዚያ የሚያልፍ ሁሉ ሰላም አያገኝም። #ሮም 3፥15-17።
ሕዝቡ ኃጢአታቸውን መናዘዛቸው
9ሕዝቡ እንዲህ ይላሉ፦ “ፍትሕ ከእኛ ርቆአል፤ ጽድቅም ወደ እኛ አይደርስም፤ ብርሃን እንዲበራልን እንፈልጋለን፤ ነገር ግን ሁሉም ጨለማ ነው፤ ስለዚህ በድቅድቅ ጨለማ እንመላለሳለን። 10በዳበሳ እንሄዳለን፤ መንገዳችንንም የምንከታተለው በዳበሳ ነው፤ በድንግዝግዝታ እንዳለን ዐይነት በቀትር እንደናቀፋለን፤ በኀያላን ሰዎችም መካከል እንደ ሞቱ ሰዎች ነን። 11ሁላችንም እንደ ድብ በመጮኽ እንደ ርግብም ምርር ብለን በማልቅስ ፍትሕንና መዳንን ለማግኘት እንጠባበቃለን፤ እነርሱ ግን ከእኛ የራቁ ስለ ሆኑ አይገኙም።
12“በደላችን በአንተ ፊት ብዙ መሆኑን ኃጢአታችን በእኛ ላይ ይመሰክራል፤ ሁልጊዜ እንበድላለን፤ መበደላችንንም እናውቃለን። 13በእግዚአብሔር ላይ ያለንን እምነት በማጓደል ዐምፀናል፤ አምላካችንን ትተን ወደ ኋላ አፈግፍገናል፤ በልባችን ውስጥ ውሸትን አውጠንጥነን ስም በማጥፋትና በከሐዲነት ገልጠናቸዋል። 14በሕዝብ አደባባይ እውነት ስለ ተሰናከለና ታማኝነት ሊገባ ስላልቻለ ፍትሕ ወደ ኋላ ተመልሶአል፤ ጽድቅም ተዳክሞአል። 15እውነት ጠፍቶአል፤ ከክፉ ሥራ የሚመለስ የሌሎች መሳለቂያ ይሆናል፤ እግዚአብሔርም ፍትሕ አለመኖሩን አይቶ አዘነ። 16ተጨቋኞችን የሚረዳ አንድ ሰው እንኳ አለመገኘቱ አስገረመው፤ ስለዚህ እነርሱን ለማዳን በኀይሉ ተጠቅሞ ድልን እንዲጐናጸፉ አደረጋቸው። #ኢሳ. 63፥5። 17እርሱ ጽድቅን እንደ ደረት ጥሩር፥ ማዳንንም እንደ ራስ ቊር ይለብሳል፤ በቀልን እንደ ልብስ ይጐናጸፋል፤ ቊጣንም እንደ ካባ ይደርባል። #ኤፌ. 6፥14፤17፤ 1ተሰ. 5፥8። 18ተቃዋሚዎቹን በመቈጣት፥ በጠላቶቹና በጠረፍ በሚኖሩት ላይ በመበቀል እንደ ተግባራቸው ይከፍላቸዋል። 19እርሱ በኀይለኛ ነፋስ እየተነዳ እንደሚመጣ ጐርፍ ስለ ሆነ በምዕራብ ያሉ ሕዝቦች የእግዚአብሔርን ስም በምሥራቅ ያሉት ክብሩን ይፈራሉ።”
20እግዚአብሔር ለሕዝቡ እንዲህ ይላል፦ “ለጽዮንና፥ ከኃጢአታቸው በንስሓ ለሚመለሱም አዳኝ ይመጣል።” #ሮም 11፥26። 21እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ከእነርሱ ጋር የሚኖረኝ ቃል ኪዳን ይህ ነው፦ ከአሁን ጀምሮ እስከ ዘለዓለም በእናንተ ላይ ያለው መንፈሴና በአንደበታችሁ ያኖርኩትን ቃሌን ለልጆቻችሁና ለልጅ ልጆቻችሁ አስተምሩ ይላል እግዚአብሔር።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ