የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 58

58
እውነተኛ ጾም
1እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ድምፅህን ሳትቈጥብ ጩኽ! ድምፅህ እንደ እምቢልታ ከፍ ይበል! ለሕዝቤ ለእስራኤል ዐመፃቸውንና ኃጢአታቸውን ንገራቸው። 2ሆኖም ዕለት በዕለት ይሹኛል፤ መንገዶቼንም ማወቅ ደስ ይላቸዋል፤ ጽድቅን እንደሚያዘወትሩና የእኔን የአምላካቸውን ትእዛዝ እንዳልተወ ሕዝብ ከእኔ ትክክለኛውን ፍርድ ይለምናሉ፤ ወደ እኔ ወደ አምላክም በመቅረብ ይደሰታሉ።”
3ሕዝቡም “እነሆ እኛ እንጾማለን፤ አንተ ግን አትመለከተንም፤ የማትመለከተንስ ከሆነ ሰውነታችንን ለምን እናዋርዳለን?” ይላሉ።
እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፦ “እነሆ እናንተ በምትጾሙበት ጊዜ የልባችሁን ፈቃድ ትፈጽማላችሁ፤ ሠራተኞቻችሁንም ሁሉ ትጨቊናላችሁ፤ 4የጾማችሁ መጨረሻው ጠብና ጭቅጭቅ ስለ ሆነ ጭካኔ በተሞላበት ቡጢ ትማታላችሁ፤ እንደዚህ አድርጋችሁ የምትጾሙት ጾም ጸሎታችሁን በላይ በሰማይ እንዲሰማ አያደርገውም። 5እናንተ በምትጾሙበት ጊዜ ሰውነታችሁን ታጐሳቊላላችሁ፤ ራሳችሁን እንደ ሸምበቆ ዝቅ ታደርጋላችሁ፤ አመድ ነስንሳችሁ፥ ማቅም አንጥፋችሁ ትተኛላችሁ? ታዲያ እናንተ ጾም የምትሉት ይህን ነውን? እኔስ በዚህ ዐይነቱ ጾም ደስ የሚለኝ ይመስላችኋልን?
6“እኔ የምደሰትበት ጾም የጭቈና ሰንሰለትና የፍትሕ መጓደል ቀንበር ታላሉ ዘንድ፥ ቀንበሩን ሰብራችሁ የተጨቈኑትን ነጻ ታወጡ ዘንድ አይደለምን? 7ምግባችሁን ከተራበ ሰው ጋር እንድትካፈሉ፥ ማደሪያ የሌለውን ድኻ በቤታችሁ እንድትቀበሉ፥ የተራቈቱትን እንድታለብሱ፥ ከቅርብ ዘመዶቻችሁም ራሳችሁን እንዳትደብቁ አይደለምን? #ማቴ. 25፥35።
8“ይህን ብታደርጉ ብርሃናችሁ እንደ ንጋት ብርሃን ያበራል፤ ፈውሳችሁም በፍጥነት ይመጣል፤ ፈራጃችሁ በፊታችሁ ይሄዳል፤ የእግዚአብሔር ክብር የኋላ ደጀን ይሆናችኋል። 9ከዚያ በኋላ ትጸልያላችሁ፤ እኔም ጸሎታችሁን እሰማለሁ፤ የእርዳታ ጩኸት ትጮኻላችሁ፤ እኔም አለሁ እላችኋለሁ፤ እናንተ የጭቈናን ቀንበር ብታስወግዱ፥ የጣት ጥቆማንና የተንኰልን ንግግር ብታቆሙ፥ 10ምግባችሁን ለተራበ ብታካፍሉ፥ የተቸገሩ ሰዎችን ፍላጎት ብታረኩ፥ ብርሃናችሁ በጨለማ ያበራል፤ ጨለማችሁም እንደ ቀትር ብርሃን ይሆናል። 11እኔ ሁልጊዜ እመራችኋለሁ፤ በድርቅም ቦታ ፍላጎታችሁን አረካለሁ፤ አጥንታችሁንም አጠነክራለሁ፤ ውሃ እንደሚጠጣ የአትክልት ቦታና ደርቆ እንደማያውቅ ምንጭ ትሆናላችሁ። 12ሕዝባችሁ ቀድሞ ፈራርሰው የነበሩትን ሁሉ እንደገና መልሶ በጥንቱ መሠረት ላይ ይሠራል፤ ስለዚህም እናንተ ‘ቅጽሮችን መልሶ የሚያንጽና ፈራርሰው የነበሩ ቤቶችን የሚያድስ ሕዝብ’ ተብላችሁ ትጠራላችሁ።”
ሰንበትን በማክበር የሚገኝ ዋጋ
13እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በተቀደሰው ቀኔ የራሳችሁን ጥቅም በማሳደድ ሰንበቴን ከመሻር ብትቈጠቡ፥ ሰንበቴን አስደሳች፥ የተከበረውንም የእኔን የእግዚአብሔርን ቀን የተከበረ ቀን ብትሉት፥ የግል ፍላጎታችሁንና የግል ጉዳያችሁን ተግባራዊ ለማድረግ በራሳችሁ አካሄድ መመራትን ትታችሁ ሰንበቴን ብታከብሩ፥ 14በእኔ በእግዚአብሔር ደስ ይላችኋል፤ በምድርም ላይ ከፍ ባለ ቦታ እንድትኖሩ አደርጋለሁ፤ ለቀድሞ አባታችሁ ለያዕቆብ ካወረስኩት ርስት በሚገኘው ምርት እንድትጠግቡ አደርጋችኋለሁ። ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ