እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ድምፅህን ሳትቈጥብ ጩኽ! ድምፅህ እንደ እምቢልታ ከፍ ይበል! ለሕዝቤ ለእስራኤል ዐመፃቸውንና ኃጢአታቸውን ንገራቸው። ሆኖም ዕለት በዕለት ይሹኛል፤ መንገዶቼንም ማወቅ ደስ ይላቸዋል፤ ጽድቅን እንደሚያዘወትሩና የእኔን የአምላካቸውን ትእዛዝ እንዳልተወ ሕዝብ ከእኔ ትክክለኛውን ፍርድ ይለምናሉ፤ ወደ እኔ ወደ አምላክም በመቅረብ ይደሰታሉ።” ሕዝቡም “እነሆ እኛ እንጾማለን፤ አንተ ግን አትመለከተንም፤ የማትመለከተንስ ከሆነ ሰውነታችንን ለምን እናዋርዳለን?” ይላሉ። እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፦ “እነሆ እናንተ በምትጾሙበት ጊዜ የልባችሁን ፈቃድ ትፈጽማላችሁ፤ ሠራተኞቻችሁንም ሁሉ ትጨቊናላችሁ፤ የጾማችሁ መጨረሻው ጠብና ጭቅጭቅ ስለ ሆነ ጭካኔ በተሞላበት ቡጢ ትማታላችሁ፤ እንደዚህ አድርጋችሁ የምትጾሙት ጾም ጸሎታችሁን በላይ በሰማይ እንዲሰማ አያደርገውም። እናንተ በምትጾሙበት ጊዜ ሰውነታችሁን ታጐሳቊላላችሁ፤ ራሳችሁን እንደ ሸምበቆ ዝቅ ታደርጋላችሁ፤ አመድ ነስንሳችሁ፥ ማቅም አንጥፋችሁ ትተኛላችሁ? ታዲያ እናንተ ጾም የምትሉት ይህን ነውን? እኔስ በዚህ ዐይነቱ ጾም ደስ የሚለኝ ይመስላችኋልን? “እኔ የምደሰትበት ጾም የጭቈና ሰንሰለትና የፍትሕ መጓደል ቀንበር ታላሉ ዘንድ፥ ቀንበሩን ሰብራችሁ የተጨቈኑትን ነጻ ታወጡ ዘንድ አይደለምን? ምግባችሁን ከተራበ ሰው ጋር እንድትካፈሉ፥ ማደሪያ የሌለውን ድኻ በቤታችሁ እንድትቀበሉ፥ የተራቈቱትን እንድታለብሱ፥ ከቅርብ ዘመዶቻችሁም ራሳችሁን እንዳትደብቁ አይደለምን? “ይህን ብታደርጉ ብርሃናችሁ እንደ ንጋት ብርሃን ያበራል፤ ፈውሳችሁም በፍጥነት ይመጣል፤ ፈራጃችሁ በፊታችሁ ይሄዳል፤ የእግዚአብሔር ክብር የኋላ ደጀን ይሆናችኋል። ከዚያ በኋላ ትጸልያላችሁ፤ እኔም ጸሎታችሁን እሰማለሁ፤ የእርዳታ ጩኸት ትጮኻላችሁ፤ እኔም አለሁ እላችኋለሁ፤ እናንተ የጭቈናን ቀንበር ብታስወግዱ፥ የጣት ጥቆማንና የተንኰልን ንግግር ብታቆሙ፥ ምግባችሁን ለተራበ ብታካፍሉ፥ የተቸገሩ ሰዎችን ፍላጎት ብታረኩ፥ ብርሃናችሁ በጨለማ ያበራል፤ ጨለማችሁም እንደ ቀትር ብርሃን ይሆናል። እኔ ሁልጊዜ እመራችኋለሁ፤ በድርቅም ቦታ ፍላጎታችሁን አረካለሁ፤ አጥንታችሁንም አጠነክራለሁ፤ ውሃ እንደሚጠጣ የአትክልት ቦታና ደርቆ እንደማያውቅ ምንጭ ትሆናላችሁ። ሕዝባችሁ ቀድሞ ፈራርሰው የነበሩትን ሁሉ እንደገና መልሶ በጥንቱ መሠረት ላይ ይሠራል፤ ስለዚህም እናንተ ‘ቅጽሮችን መልሶ የሚያንጽና ፈራርሰው የነበሩ ቤቶችን የሚያድስ ሕዝብ’ ተብላችሁ ትጠራላችሁ።”
ትንቢተ ኢሳይያስ 58 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ኢሳይያስ 58:1-12
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos