ትንቢተ ኢሳይያስ 57
57
የእስራኤል ጣዖት አምልኮ መወገዝ
1ጻድቃን ሲሞቱ ማንም ትኲረት አይሰጠውም፤ ደጋግ ሰዎች በሞት ሲወሰዱ ከክፉ ነገር እንዲድኑ የተወሰዱ መሆናቸውን ማንም ሰው ሊያስተውለው አይችልም። 2ቀጥተኛ ሕይወትን የሚኖሩ ሰዎች ሰላም ይኖራቸዋል፤ በሚሞቱበትም ጊዜ ዕረፍትን ያገኛሉ።
3ከአስማተኞች፥ ከአመንዝራዎችና ከዘማውያን የማትሻሉ እናንተ ወደ እዚህ ቅረቡ! 4እናንተ የምታፌዙ፥ አፋችሁን የምትከፍቱትና ምላሳችሁን የምታወጡት በማን ላይ ነው? እናንተ ዐመፀኞችና ሐሰተኞች ልጆች አይደላችሁምን? 5እናንተ በዋርካ ዛፎች መካከልና በየለምለሙ ዛፍ ሥር በፍትወት የምትቃጠሉ ናችሁ፤ እንዲሁም በሸለቆዎች ውስጥ በቋጥኞች መካከል ልጆቻችሁን ለዕርድ ታቀርባላችሁ። 6ከሸለቆ ለስላሳ ድንጋዮች መካከል መርጣችሁ አማልክታችን ናቸው በማለት የመጠጥና የእህል ቊርባን ታቀርቡላቸዋላችሁ። በዚህ ነገር አልቈጣምን? 7በከፍተኛ ተራራ ጫፍ ላይ ዝሙት ለመፈጸምና መሥዋዕት ለማቅረብ ትወጣላችሁ። 8ከበራችሁና ከመቃኖቹ በስተጀርባ የጣዖት ምስሎችን አስቀምጣችኋል፤ እኔን ትታችሁ ዝሙት ለመፈጸም ወደ አልጋዎቻችሁ ወጥታችኋል፤ በዝሙት ዋጋ ተደራድራችሁ ፍትወታችሁን ታረካላችሁ። 9ብዙ ዘይትና ሽቶ ተቀብታችሁ ሞሌክ ወደ ተባለው ጣዖት ሄዳችሁ፤ የምታመልኳቸውን ጣዖቶች ለመፈለግ መልእክተኞቻችሁን ወደ ሩቅ ቦታ ወደ ሙታን ዓለም እንኳ ሳይቀር ላካችሁ። 10ከብዙ መንከራተታችሁ የተነሣ ትደክማላችሁ፤ ሆኖም ግን ፍላጎታችሁ በጣም ስለ ተነሣሣ “ጠቃሚ አይደለም” ብላችሁ አላቆማችሁም።
11“እኔን ባለማስታወስና ስለ እኔ ባለማሰብ ውሸት የተናገራችሁት ማንን ፈርታችሁ ነው? እኔን ያልፈራችሁኝ ለብዙ ጊዜ ዝም ስለልኩና እንዳላየ ስለሆንኩ ነውን? 12ትክክል ናቸው ብላችሁ የምታስቡአቸውን ሥራዎቻችሁን አጋልጣለሁ፤ ጣዖቶቻችሁም ሊረዱአችሁ አይችሉም። 13ርዳታ ለማግኘት በምትጮኹበት ጊዜ እስቲ የሰበሰባችኋቸው ጣዖቶቻችሁ ያድኑአችሁ! እነርሱን የነፋስ ሽውታ ያስወግዳቸዋል፤ እስትንፋስም ይወስዳቸዋል፤ በእኔ የሚተማመን ግን ምድሪቱ የእርሱ ትሆናለች፤ የተቀደሰ ተራራዬንም ርስት ያደርጋል።”
እግዚአብሔር ሕዝቡን ለመርዳትና ለመፈወስ የሰጠው ተስፋ
14እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “አስተካክሉ፥ አስተካክሉ፥ መንገዱን ጥረጉ! ሕዝቤ ከሚሄዱበት መንገድ መሰናክሉን አስወግዱ!”
15ከፍተኛውና ከሁሉ የላቀው፥ ለዘለዓለም የሚኖር ቅዱሱ እንዲህ ይላል፦ “እኔ በተቀደሰና በከፍተኛ ቦታ፥ እንዲሁም ልባቸው ከተሰበረና መንፈሳቸው ትሑት ከሆኑት ጋር እኖራለሁ፤ ይኸውም ትሑት መንፈሳቸውንና የተሰበረ ልባቸውን ለማደስ ነው። 16እኔ ዘወትር ሰውን አልወቅስም፤ ሁልጊዜም አልቈጣም፤ ይህን ባደርግ ኖሮ፥ የፈጠርኳቸው ሰዎች መንፈሳቸው ይዝል ነበር። 17ክፉ በሆነው ስግብግብነታቸው ምክንያት በእነርሱ ላይ ተቈጥቼ ነበር፤ እንዲሁም እነርሱን ቀጥቼ ተለይቼአቸው ነበር፤ እነርሱም ወደ ራሳቸው መንገድ ተመለሱ።
18“እኔ ሥራቸውን ሁሉ ተመልክቼአለሁ፤ ይሁን እንጂ እፈውሳቸዋለሁ፤ እመራቸዋለሁ፤ እኔ ለእነርሱና ስለ እነርሱ ለሚያለቅሱት ሙሉ መጽናናትን እሰጣለሁ። 19በሩቅና በቅርብ ላሉትም ሁሉ ሰላም ይሁን! እኔ ሕዝቤን እፈውሳለሁ፤ 20ክፉ ሰዎች ግን እንደሚናወጥ ባሕር ናቸው፤ ውሃውም ቈሻሻውንና ጭቃውን ቀስቅሶ ያወጣል እንጂ ጸጥ አይልም። 21ለክፉዎች ሰላም የላቸውም” ይላል አምላኬ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 57: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997