ትንቢተ ኢሳይያስ 48
48
የእግዚአብሔር ፈጣሪነትና አዳኝነት
1በእስራኤል ስም የምትጠሩ፥ ከይሁዳ ወገን የሆናችሁ፥
እናንተ የያዕቆብ ልጆች! ይህን ስሙ።
እናንተ በታማኝነትና በእውነት ሳይሆን፥
የእስራኤልን አምላክ እናመልካለን ትላላችሁ፤
በእግዚአብሔር ስምም ትምላላችሁ።
2ራሳችሁም “የቅድስቲቱ ከተማ ነዋሪዎች ነን፤
በሠራዊት ጌታ በእስራኤል አምላክ እንተማመናለን” ብላችሁ ትመካላችሁ።
3እግዚአብሔር ለእስራኤል እንዲህ ይላል፦
“ወደ ፊት ስለሚሆነው ነገር ከብዙ ጊዜ በፊት ተናገርኩ፤
እርሱንም በፍጥነት እንዲከናወን አደረግሁ።
4እንደማይተጣጠፍ ነሐስና እንደ ጠንካራ ብረት
የማትመለሱ እልኸኞች መሆናችሁን ዐውቃለሁ።
5ስለ እነዚህ ነገሮች ሁሉ አስቀድሜ ነግሬአችኋለሁ፤
ከመፈጸማቸውም በፊት አስታውቄአችኋለሁ፤
ይህንንም ያደረግኹት ‘ጣዖቶቻችን ይህን አደረጉ፤
የእንጨትና የብረት ምስሎቻችን ይህን ወሰኑ’ እንዳትሉ ነው።
6“እኔ የተናገርኩትን ሰምታችኋል፤
ይህም መፈጸሙን አይታችኋል፤
አስተውሉትና እውነተኛነቱን አረጋግጡ፤
ከአሁን ጀምሮ ቀድሞ ተሰውሮ የነበረ
እናንተ ያላወቃችሁትን አዲስ ነገር
ወደፊት አሳያችኋለሁ።
7እነርሱ ከብዙ ጊዜ በፊት ሳይሆን አሁን የተፈጠሩ ናቸው፤
እናንተም ‘ቀደም ብለን ዐውቀናቸዋል’ እንዳትሉ
ከአሁን በፊት ከቶ አልሰማችኋቸውም።
8እኔ የምናገረውን አትሰሙም፤ ለማወቅም አትፈልጉም፤
ከጥንት ጀምሮ ጆሮአችሁ የተደፈነ ነው፤
ይህም የሆነው እናንተ በጣም ከዳተኞች መሆናችሁንና
ከተወለዳችሁ ጀምሮ ዐመፀኞች ተብላችሁ መጠራታችሁን ዐውቃለሁ።
9“ስለ ስሜ ክብር ቊጣዬን አዘገያለሁ፤
ሰዎችም ያመሰግኑኝ ዘንድ ቊጣዬ እንዳያጠፋችሁ እገታዋለሁ።
10እንደ ብር ሳይሆን በመከራ እሳት አንጥሬአችኋለሁ፥
በችግር እቶንም ፈትኜአችኋለሁ።
11ስለ እኔ ስለ ራሴ ይህን አደርገዋለሁ፤
ስሜስ ለምን ይነቀፋል?
ክብሬንም ለማንም አልሰጥም።”
እግዚአብሔር የመረጠው አገልጋይ
12እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“የጠራኋችሁ የያዕቆብ ልጆች እስራኤላውያን ሆይ! አድምጡ!
እኔ ብቻ አምላክ ነኝ፤ እኔ የመጀመሪያውና የመጨረሻው ነኝ። #ኢሳ. 44፥6፤ ራዕ. 1፥17፤ 22፥13።
13እኔ ምድርን መሠረትኩ፤
ሰማያትንም ዘረጋሁ።
ስጠራቸውም ይገኛሉ።
14“ሁላችሁም ተሰብስባችሁ ኑና አድምጡ!
ስለ እነዚህ ነገሮች አስቀድሞ የተናገረ
ከጣዖቶች መካከል የትኛው ነው?
የእግዚአብሔር ተመራጭ በባቢሎን ላይ ዓላማውን ይፈጽማል።
ኀይሉም በባቢሎናውያን ላይ ይሆናል።
15እኔ ራሴ ተናግሬአለሁ፤ ጠርቼዋለሁም፤
እኔ አመጣዋለሁ፤ የእርሱም ተልእኮ የተሳካ ይሆናል።
16ወደ እኔ ቀርባችሁ ይህን ስሙ፤
ከመጀመሪያ ጀምሮ የተናገርኩት በምሥጢር አይደለም፤
ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ እኔ እዚያ ነበርኩ።”
አሁንም ጌታ እግዚአብሔርና መንፈሱ ልከውኛል።
17እናንተን የሚያድን የእስራኤል ቅዱስ
እግዚአብሔር አምላክ እንዲህ ይላል፤
“የሚጠቅምህን ሁሉ የማስተምርህና
ልትሄድበት የሚገባህን መንገድ የምመራህ
እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ።
18“ትእዛዞቼን በጥንቃቄ ሰምታችሁ ቢሆንማ ኖሮ፥
በረከታችሁ እንደማይደርቅ የወንዝ ውሃ፥
ጽድቃችሁም እንደ ባሕር ሞገድ በብዛት በመጣላችሁ ነበር!
19ሕዝባችሁም ባልተደመሰሰና ስማችሁም
ባልተረሳ ነበር!”
20እንግዲህ ከባቢሎን ወጥታችሁ ሽሹ፤
“እግዚአብሔር አገልጋዩን እስራኤልን አድኖአል” የሚለውን
የምሥራች ቃል በደስታ አብሥሩ፤
በየስፍራውም እንዲታወቅ አድርጉ። #ራዕ. 18፥4።
21እግዚአብሔር በምድረ በዳ በመራቸው ጊዜ ውሃ አልጠማቸውም፤
ይልቁንስ ውሃ ከአለት እንዲፈልቅላቸው አደረገ።
አለቱን ከፍሎ ውሃ አጐረፈላቸው።
22“ለክፉዎች ሰላም የላቸውም” ይላል እግዚአብሔር። #ኢሳ. 57፥21።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 48: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997