የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 49

49
የእግዚአብሔር አገልጋይ ተልእኮ
1በደሴት የምትኖሩ ሕዝቦች አድምጡኝ!
በሩቅ አገር ያላችሁም ሰዎች አስተውሉ፤
እግዚአብሔር ከመወለዴ በፊት ጠራኝ፤
በእናቴ ማሕፀን እያለሁ ስም አወጣልኝ። #ኤር. 1፥5።
2አንደበቴን እንደ ሰይፍ የተሳለ አደረገው፤
በእጁ ጥላ ሥርም ሰወረኝ፤
እንደ ተሳለ ፍላጻ አድርጎ በሰገባው ውስጥ ደበቀኝ። #ዕብ. 4፥12፤ ራዕ. 1፥16።
3እርሱም “እስራኤል ሆይ! አንተ አገልጋዬ ነህ፤
በአንተ ምክንያት ሕዝቦች ያከብሩኛል” አለኝ።
4እኔ ግን “በከንቱ ለፋሁ፤
ያለ ጥቅም በከንቱ ጒልበቴን አባከንሁ፤
ሆኖም ጉዳዬ በእግዚአብሔር ዘንድ ነው፤
የድካሜም ዋጋ ከአምላኬ ጋር ነው” አልኩ።
5ገና በእናቴ ማሕፀን ሳለሁ እግዚአብሔር መርጦኛል፤
የተበታተኑትን የያዕቆብን ልጆች እስራኤላውያንን ለመሰብሰብ አገልጋዩ አድርጎኛል።
እኔ በእግዚአብሔር ዘንድ የተከበርኩ ነኝ፤
አምላኬም ኀይል ሆኖልኛል።
6እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፦
“የያዕቆብን ነገዶች ክብር እንደገና ለማንሣትና
የተረፉትን እስራኤላውያን ለመመለስ አገልጋዬ ሆነህ መሥራት ብቻ አይበቃም።
ከዚህ የበለጠ ግን አዳኝነቴ እስከ ምድር ዳርቻ ይደርስ ዘንድ
አንተ ለሕዝቦች ሁሉ ብርሃን እንድትሆን አደርግሃለሁ።” ይላል። #ኢሳ. 42፥6፤ ሉቃ. 2፥32፤ ሐ.ሥ. 13፥47፤ 26፥23።
7በሕዝቦች ዘንድ በጣም ለተናቅህና ለተጠላህ፥
ለገዢዎችም አገልጋይ ለሆንክ ለአንተ፥
አዳኙ የእስራኤል ቅዱስ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“ነገሥታት ሲያዩህ ይነሡልሃል፤
ልዑላንም ይሰግዱልሃል፤
ይህም የሚሆነው በመረጠህ በታማኙ በእስራኤል ቅዱስ በእግዚአብሔር ምክንያት ነው።”
የኢየሩሳሌም እንደገና መሠራት
8እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“በመረጥኩት ሰዓት ለጸሎትህ መልስ እሰጥሃለሁ፤
በመዳንም ቀን እረዳሃለሁ፤
ምድሪቱን መልሰህ እንድታቋቋምና
ውድማ የሆነውን መሬት እንድታከፋፍል
ቃል ኪዳን አድርጌ ለሕዝቡ ሰጥቼሃለሁ። #2ቆሮ. 6፥2።
9አንተም እስረኞችን ‘በነጻ ሂዱ!’
በጨለማ ያሉትን ‘ወደ ብርሃን ውጡ’ ትላቸዋለህ፤
በየመንገዱ ምግብ ያገኛሉ፤
ደረቅ በነበረውም ተራራ ላይ እንደ ፍየል ይሰማራሉ።
10መራብና መጠማትም አይደርስባቸውም፤
የሚያቃጥል ነፋስ ወይም ፀሐይ አይጐዳቸውም፤
ይህም የሚሆነው የሚራራላቸው እርሱ የውሃ ምንጭ ወደሚገኝበት ቦታ ስለሚመራቸው ነው። #ራዕ. 7፥16-17።
11“ተራሮቼን ደልድዬ መንገድ አደርጋለሁ፤
ጐዳናዎቼም ከፍ ይላሉ።
12ሕዝቦቼ ከሩቅ አገሮች ይመጣሉ፤
ከሰሜንና ከምዕራብ
እንዲሁም ከሲኒም።”#49፥12 ሲኒም፦ በአሁኑ ጊዜ አስዋን የሚባለው የግብጽ ከተማ ነው።
13እግዚአብሔር ሕዝቡን ስለሚያጽናና እና ለሚሠቃዩትም ስለሚራራ
ሰማያት ሆይ! ዘምሩ፤ ምድር ሆይ! ደስ ይበልሽ፤
ተራራዎች ሆይ! እልል በሉ።
14የኢየሩሳሌም ሕዝብ ግን፥
“እግዚአብሔር ትቶናል፤ ጌታዬም ረስቶናል” አሉ።
15እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል ይመልሳል፦
“እናት የምታጠባውን ልጅዋን ልትረሳ ትችላለችን?
ወይስ ለወለደችው ልጅ አትራራምን?
እርስዋ እንኳ ብትረሳ
እኔ ግን እናንተን አልረሳም።
16ኢየሩሳሌም ሆይ! እነሆ፥ በእጄ መዳፍ ላይ ቀርጬሻለሁ፤
ቅጥሮችሽንም ዘወትር አስታውሳለሁ።
17“አንቺን የሚገነቡ ፈጣኖች ናቸው፤
ያወደሙሽ ግን ከአንቺ ርቀው ይሄዳሉ።
18ቀና ብለሽ ዙሪያሽን ተመልከቺ፤
ልጆችሽ ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ፤
እኔ እግዚአብሔር ሕያው እንደ መሆኔ እንዲህ እላለሁ፦
‘ሁሉንም እንደ ልብስ ትለብሺአቸዋለሽ፤
ሙሽራ በጌጣጌጥ እንደምታጌጥ አንቺም በእነርሱ ታጌጪአለሽ።’
19“ ‘ፈራርሰሽ ባድማ እንድትሆኚ፥
ምድርሽም ጠፍ እንዲሆን ቢያደርጉሽም እንኳ፥
አሁን አንቺ ተመልሰው ለሚመጡ ለነዋሪዎችሽ ጠባብ ትሆኚአለሽ፤
የአፈራረሱሽም ከአንቺ ርቀው ይሄዳሉ።’
20በስደት የተወለዱ ልጆችሽ
‘ይህ ቦታ ለእኛ በጣም ጠባብ ስለ ሆነ
የምንኖርበት ሰፊ ቦታ ስጪን’ ይሉሻል።
21ከዚህ በኋላ አንቺም በልብሽ እንዲህ ትያለሽ፦
‘እነዚህን ልጆች ማን ወለደልኝ?
ብዙ ልጆቼን አጥቼና የወላድ መኻን ሆኜ ነበር፤
ተሰድጄ፥ ተቀባይነትም አጥቼ ነበር፤
ታዲያ እነዚህን ልጆች ያሳደጋቸው ማነው?
እኔ ብቻዬን ቀርቼ ነበር፤
እንግዲህ እነዚህ ልጆች ከወዴት መጡ?’ ”
22ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“ወንዶች ልጆችሽን በክንዳቸው፥ ሴቶች ልጆችሽንም
በትከሻቸው ተሸክመው ያመጡ ዘንድ
ለመንግሥታት ምልክት እሰጣለሁ፤
ለሕዝቦችም ዐርማን አነሣለሁ።
23ነገሥታት አሳዳጊ አባቶችሽ ይሆናሉ፤
እቴጌዎቻቸውም ሞግዚቶችሽ ይሆናሉ፤
ግንባራቸውንም ወደ ምድር ዝቅ አድርገው ይሰግዱልሻል።
የእግርሽንም ትቢያ ይልሳሉ፤
ከዚህም የተነሣ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቂአለሽ፤
የእኔን ርዳታ ለማግኘት የሚጠባበቁ ከቶ አያፍሩም።”
24ከጀግና እጅ ምርኮን መውሰድ ይቻላልን?
ወይስ ከጨካኝ ሰው እጅ ምርኮኛን ማስለቀቅ ይቻላልን?
25እግዚአብሔር ግን እንዲህ ይላል፦
“አንቺን የሚቃወሙሽን እኔ ስለምቃወም፥
ጀግና የያዘው ምርኮኛ እንኳ ይወሰዳል፤
ከጨካኝ እጅም ምርኮ ይለቀቃል፤
እኔም ልጆችሽን አድናለሁ።
26ጨቋኞችሽ የገዛ ሥጋቸውን እንዲበሉ አደርጋለሁ፤
በወይን ጠጅ እንደሚሰክሩ የገዛ ደማቸውን ጠጥተው እንዲሰክሩ አደርጋለሁ።
ከዚህም የተነሣ እኔ እግዚአብሔር አዳኝሽና ታዳጊሽ
የእስራኤል ኀያል አምላክ መሆኔን የዓለም ሕዝብ ሁሉ ያውቃል።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ