የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 50

50
1እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“ወንድ ሚስቱን ፈቶ እንደሚያባርር
እኔ እናንተን ሕዝቤን ያባረርኩ ይመስላችኋልን?
ይህስ ከሆነ የፍችው ደብዳቤ የት አለ?
ሰው ልጆቹን ለባርነት እንደሚሸጥ
እኔም እናንተን ለምርኮ አሳልፌ የሸጥኳችሁ ይመስላችኋልን?
ከሆነስ ለማንኛውም አበዳሪዬ ሸጥኳችሁ?
እናንተ ለምርኮ የተሰጣችሁት በኃጢአታችሁ ምክንያት ነው፤
የተሰደዳችሁትም በፈጸማችሁት በደል ነው።
2“እኔ በመጣሁ ጊዜ ማንም ሰው አለመኖሩ ለምንድን ነው?
በጠራሁም ጊዜ ማንም ሰው መልስ ያልሰጠኝ ለምንድን ነው?
እኔ ለመታደግ አልችልምን?
ለማዳንስ ኀይል የለኝምን?
በተግሣጼ ብቻ ባሕርን አደርቃለሁ፤
ወንዞችንም ወደ ምድረ በዳነት እለውጣለሁ፤
ዓሣዎቻቸውም ውሃ ከማጣት የተነሣ ሞተው ይበሰብሳሉ።
3ሰማያትን ጨለማ አለብሳቸዋለሁ
መጋረጃቸውም ማቅ ይሆናል።”
4ደካሞችን በቃል ማጽናትን ዐውቅ ዘንድ
ጌታ እግዚአብሔር የምሁርን አንደበት ሰጥቶኛል፤
በየማለዳው ከእንቅልፍ ያነቃኛል፤
እንደ ተማሪም አዳምጥ ዘንድ ጆሮዬን ይከፍታል።
5ጌታ እግዚአብሔር ማስተዋልን ሰጥቶኛል፤
እኔም ዐመፀኛ ሆኜ ከእርሱ አልራቅሁም።
6ለሚገርፉኝ ጀርባዬን፥
ጢሜንም ለሚነጩ ጒንጬን ሰጠኋቸው፤
ከሚሰድቡኝና ከሚተፉብኝ ፊቴን አላዞርኩም። #ማቴ. 26፥67፤ ማር. 14፥65።
7ጌታ እግዚአብሔር ስለሚረዳኝ አልተዋረድኩም፤
ራሴን እንደ ጠንካራ ድንጋይ አበረታሁ፤
እንደማላፍርም ዐውቃለሁ።
8የሚፈርድልኝ እግዚአብሔር ቅርብ ነው፤
ታዲያ ማን ይከሰኛል?
የሚከሰኝ ካለ ፊት ለፊት እንገናኝ፤
እስቲ ይቋቋመኝ።
9የሚረዳኝ ጌታ እግዚአብሔር ነው፤
ማን ይፈርድብኛል?
ከሳሾቼ እንደ ልብስ ያረጃሉ፤
ብልም ይበላቸዋል። #ሮም 8፥33-34።
10ከእናንተ መካከል እግዚአብሔርን የሚፈራና
ለአገልጋዩ ቃል የሚታዘዝ ማነው?
ብርሃን የሌለው በጨለማ የሚመላለስ
በእግዚአብሔር ይታመን፤
እምነቱንም በአምላኩ ላይ ይጣል።
11እናንተ ሁላችሁም ነገር በሰው ላይ እንደ እሳት የምታነዱና
እንደ ችቦ የምትለኲሱ ናችሁ፤
ባነደዳችሁት እሳት ነበልባል ውስጥና በለኰሳችሁት ችቦ ትጠፋላችሁ
ይህንንም ቅጣት የምትቀበሉት ከእኔ ነው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ