ትንቢተ ኢሳይያስ 32:1-8

ትንቢተ ኢሳይያስ 32:1-8 አማ05

በጽድቅ የሚያስተዳድር ንጉሥ የሚነሣበት ጊዜ ይመጣል፤ ሹማምንቱም በትክክል ይፈርዳሉ። ከእነርሱ እያንዳንዱ ከነፋስ እንደሚከለሉበትና ከወጀብ እንደሚሰወሩበት መጠጊያ ይሆናል፤ በበረሓ እንደሚፈስሱ ጅረቶችና በምድረ በዳ እንደሚገኝ እንደ ትልቅ አለት መጠለያ ይሆናሉ። ከዚህ በኋላ የሚያዩ ሰዎች ዐይኖች አይጨፈኑም፤ ለመስማት የሚችሉ ሰዎች ጆሮዎችም ያዳምጣሉ። ችኲሎች የነበሩ በትዕግሥት የሚያመዛዝኑ ይሆናሉ፤ ተብታባ አንደበት የነበራቸው አንደበተ ርቱዖች ይሆናሉ፤ ንግግራቸውም ግልጥ ይሆናል። ከእንግዲህ ወዲህ ሞኞች ጨዋዎች አይባሉም፤ ባለጌዎችም ክብር አይሰጣቸውም። ሞኞች የሞኝነትን ንግግር ይናገራሉ፤ አእምሮአቸውም በደልን ያሤራል፤ ስለ እግዚአብሔር ስሕተተኛ ንግግርን በማሠራጨት ክሕደትን ያስፋፋል። የተራቡትን አያጠግቡም። የባለጌዎች ሥራ ክፉ ነው፤ ምንም ያኽል የድኾች አቤቱታ ትክክል ቢሆን ውሸት በመናገር ድኾችን ለማጥፋት ክፉ ዕቅድ ያቅዳሉ። ጨዋ ሰው ግን የጨዋነት ሥራውን በታማኝነት ያቅዳል፤ በጨዋነቱም ጸንቶ ይኖራል።