ኢሳይያስ 32:1-8
ኢሳይያስ 32:1-8 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እነሆ፥ ጻድቅ ንጉሥ ይነግሣል፤ መሳፍንትም በፍርድ ይገዛሉ። ሰውም ቃሉን ይሰውራል፤ በውኃ እንደሚጠልቅም ይሰወራል፤ ክብሩም በደረቅ ምድር እንደሚፈስስ ውኃ በጽዮን ይገለጣል። እንግዲህ በሰው አይታመኑም፤ በጆሮአቸው ያዳምጣሉ እንጂ። የደካሞች ሰዎች ልብ ዕውቀትን ትሰማለች፤ የተብታቦችም ምላስ ፈጥና የሰላምን ነገር ትማራለች። ከእንግዲህ ወዲህ ሰነፍን አለቃ ይሆን ዘንድ ግድ አይሉትም፤ ከእንግዲህ ሎሌህ ዝም በል አይልህም። ሰነፍ ግን ስንፍናን ይናገራል፤ ልቡም ዐመፅን ያደርግ ዘንድ፥ በእግዚአብሔር ላይ ስሕተትን ይናገር ዘንድ፥ የተራበችውንም ሰውነት ይበትን ዘንድ፥ የተጠማችንም ነፍስ ባዶ ያደርግ ዘንድ ከንቱን ያስባል። በዐመፃቸው ነገር ድሃውን ይገድሉት ዘንድ፥ የድሆችንም ፍርድ ይገለብጡ ዘንድ የክፉዎች ሕሊና ዐመፅን ትመክራለች። ጻድቃን ግን ጥበብን ይመክራሉ፤ ምክራቸውም ትጸናለች።
ኢሳይያስ 32:1-8 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እነሆ፤ ንጉሥ በጽድቅ ይነግሣል፤ ገዦችም በፍትሕ ይገዛሉ። እያንዳንዱ ሰው ከነፋስ መከለያ፣ ከወጀብም መጠጊያ ይሆናል። በበረሓም እንደ ውሃ ምንጭ፣ በተጠማም ምድር እንደ ትልቅ ቋጥኝ ጥላ ይሆናል። የሚያዩ ሰዎች ዐይን ከእንግዲህ አይጨፈንም፤ የሚሰሙም ጆሮዎች ነቅተው ያደምጣሉ። የችኵል አእምሮ ያውቃል፤ ያስተውላልም፤ የተብታባም ምላስ የተፈታ ይሆናል፤ አጥርቶም ይናገራል። ከእንግዲህ ሰነፍ ጨዋ አይባልም፤ ጋጠወጥም አይከበርም። ሰነፍ ስንፍናን ይናገራል፤ አእምሮው ክፋትን ያውጠነጥናል፤ ፈሪሀ እግዚአብሔር የሌለበትን አድራጎት ይፈጽማል፤ በእግዚአብሔርም ላይ የስሕተት ቃል ይናገራል፤ ለተራበ ምግብ ይከለክላል፤ ለተጠማ ውሃ አይሰጥም። የጋጠወጥ ዘዴ ክፉ ነው፤ የችግረኛም አቤቱታ ትክክል ቢሆን፣ ድኻን በሐሰት ለማጥፋት፣ ክፋት ያውጠነጥናል። ጨዋ ግን ሐሳቡም ጨዋ ነው፤ በጨዋነት ምግባርም ጸንቶ ይገኛል።
ኢሳይያስ 32:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እነሆ፥ ንጉሥ በጽድቅ ይነግሣል፥ መሳፍንትም በፍርድ ይገዛሉ። ሰውም ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ ከዐውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ፥ በጥም ቦታም እንደ ወንዝ ፈሳሽ፥ በበረሃም አገር እንደ ትልቅ ድንጋይ ጥላ ይሆናል። የሚያዩትም ሰዎች ዓይኖች አይጨፈኑም፥ የሚሰሙትም ጆሮዎች ያደምጣሉ። ጥንቃቄ የሌላቸው ሰዎች ልብ እውቀትን ታስተውላለች፥ የተብታቦችም ምላስ ደኅና አድርጋ ትናገራለች። ከእንግዲህ ወዲህ ሰነፍ ከበርቴ ተብሎ አይጠራም፥ ንፉግም ለጋስ አይባልም። ሰነፍ ግን ስንፍናን ይናገራል፥ ልቡም ዝንጉነትን ይፈጽም ዘንድ በእግዚአብሔርም ላይ ስህተትን ይናገር ዘንድ፥ የተራበችውንም ሰውነት ባዶ ያደርግ ዘንድ ከተጠማም ሰው መጠጥን ይቈርጥ ዘንድ በደልን ይሠራል። የንፉግም ዕቃ ክፉ ናት፥ ችግረኛ ቅን ነገርን በተናገረ ጊዜ እንኳን እርሱ በሐሰት ቃል ድሀውን ያጠፋ ዘንድ ክፉን አሳብ ያስባል። ከበርቴ ሰው ግን ለመከበር ያስባል፥ ለመከበርም ጸንቶ ይኖራል።
ኢሳይያስ 32:1-8 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በጽድቅ የሚያስተዳድር ንጉሥ የሚነሣበት ጊዜ ይመጣል፤ ሹማምንቱም በትክክል ይፈርዳሉ። ከእነርሱ እያንዳንዱ ከነፋስ እንደሚከለሉበትና ከወጀብ እንደሚሰወሩበት መጠጊያ ይሆናል፤ በበረሓ እንደሚፈስሱ ጅረቶችና በምድረ በዳ እንደሚገኝ እንደ ትልቅ አለት መጠለያ ይሆናሉ። ከዚህ በኋላ የሚያዩ ሰዎች ዐይኖች አይጨፈኑም፤ ለመስማት የሚችሉ ሰዎች ጆሮዎችም ያዳምጣሉ። ችኲሎች የነበሩ በትዕግሥት የሚያመዛዝኑ ይሆናሉ፤ ተብታባ አንደበት የነበራቸው አንደበተ ርቱዖች ይሆናሉ፤ ንግግራቸውም ግልጥ ይሆናል። ከእንግዲህ ወዲህ ሞኞች ጨዋዎች አይባሉም፤ ባለጌዎችም ክብር አይሰጣቸውም። ሞኞች የሞኝነትን ንግግር ይናገራሉ፤ አእምሮአቸውም በደልን ያሤራል፤ ስለ እግዚአብሔር ስሕተተኛ ንግግርን በማሠራጨት ክሕደትን ያስፋፋል። የተራቡትን አያጠግቡም። የባለጌዎች ሥራ ክፉ ነው፤ ምንም ያኽል የድኾች አቤቱታ ትክክል ቢሆን ውሸት በመናገር ድኾችን ለማጥፋት ክፉ ዕቅድ ያቅዳሉ። ጨዋ ሰው ግን የጨዋነት ሥራውን በታማኝነት ያቅዳል፤ በጨዋነቱም ጸንቶ ይኖራል።
ኢሳይያስ 32:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እነሆ፥ ንጉሥ በጽድቅ ይነግሣል፥ መሳፍንትም በፍትህ ያስተዳድራሉ። ሰውም ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ ከዐውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ፥ በጥም ቦታም እንደ ወንዝ ፈሳሽ፥ በበረሃም አገር እንደ ትልቅ ቋጥኝ ጥላ ይሆናል። የሚያዩትም ሰዎች ዐይኖች አይጨፈኑም፤ የሚሰሙትም ጆሮዎች ያደምጣሉ። ጥንቃቄ የሌላቸው ሰዎች ልብ እውቀትን ታስተውላለች፤ የተብታቦችም ምላስ ተፍታታና ደኅና አድርጋ ትናገራለች። ከእንግዲህ ወዲህ ሰነፍ ጨዋ ተብሎ አይጠራም፤ ሸንጋይ ሰው የተከበረ አይባልም። ሰነፍ ግን የስንፍናን ነገር ይናገራል፤ ልቡም በጌታም ላይ ስህተትን ለመናገር፥ የተራበችውንም ሰውነት ረሃቡን እንዳያስታግስ፥ የተጠማም ሰው ጥሙን እንዳይቆርጥ በደልን ለመሥራት ክፋትን ያቅዳል። የሸንጋይ ሽንገላ ክፉ ናት፤ የችግረኛም አቤቱታ ትክክል ቢሆንም እንኳን በሐሰት ቃል ድሀውን ለማጥፋት ክፉን አሳብ ያስባል። ከበርቴ ሰው ግን ለመከበር ያስባል፤ ለመከበርም ጸንቶ ይኖራል።