ትንቢተ ኢሳይያስ 29
29
የዳዊት ከተማ ለሆነችው ለኢየሩሳሌም ወዮላት
1አሪኤል ተብላ ለምትጠራው ዳዊት ለሠፈረባት ለኢየሩሳሌም ከተማ ወዮላት! ዓመቶች ይደጋገሙ፤ በዓላትም በየዓመቱ ይከበሩ። #29፥1 አሪኤል፦ በዕብራይስጥ የእግዚአብሔር መሠዊያ ማለት ነው። 2ከዚያ በኋላ ግን እኔ እግዚአብሔር “የእግዚአብሔር መሠዊያ” ተብላ የምትጠራውን የእስራኤል ከተማ አስጨንቃለሁ፤ እዚያም ሐዘንና የለቅሶ ዋይታ ይሆናል፤ ከተማይቱም በደም እንደ ተሸፈነ መሠዊያ ትሆናለች። 3በዙሪያውም ግንብና ምሽግ ሠርቼ አስጨንቃታለሁ። በየመጠበቂያው ላይ ጠባቂዎችን አቆማለሁ። በቅጥርም መወጣጫ አሠራለሁ። 4ካለችበት ከጥልቁ ጒድጓድ ትናገራለች፤ ከታች ከትቢያ ውስጥ ንግግርዋ ይመጣል፤ ድምፅዋም እንደ ምትሐት ከምድረ በዳ ይወጣል፤ ከአዋራ ውስጥም ዝቅ ያለ ድምፅዋ ይሰማል።
5ኢየሩሳሌም ሆይ! በአንቺ ላይ በጠላትነት የሚነሡ የጠላት ሠራዊት ሁሉ እንደ ትቢያ በነው ይጠፋሉ፤ እጅግ የሚያስፈሩ ሠራዊቶቻቸውም ሳይታሰቡ በድንገት በነፋስ እንደሚወሰድ ገለባ ይሆናሉ። 6የሠራዊት ጌታ አምላክ ነጐድጓድን፥ የመሬት መናወጥን፥ ታላቅ ድምፅን፥ ዐውሎ ነፋስን፥ ሞገድንና የሚባላ የእሳት ነበልባልን በጠላቶችሽ ላይ በመላክ አንቺን ይታደግሻል። 7የእግዚአብሔር መሠዊያ የሆነችውን ከተማ ለማጥቃት የሚመጡ የመንግሥታት ሠራዊቶች ሁሉ ከነጦር መሣሪያዎቻቸው ይደመሰሳሉ፤ እንደ ሕልም ወይም በእንቅልፍ ልብ እንደሚታሰብ ነገር የተረሱ ይሆናሉ። 8በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ በመጣል የተሰበሰቡ መንግሥታት ሁሉ በሕልሙ ሲበላ ዐድሮ ጠዋት በነቃ ጊዜ ምንም ያልቀመሰ ረኃብተኛ መሆኑንና እንዲሁም በሕልሙ ሲጠጣ ዐድሮ ጧት በነቃ ጊዜ ጒሮሮው በውሃ ጥም ደርቆ እንደሚያገኘው ሰው ይሆናሉ።
የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መናቅ የሚያስከትለው ቅጣት
9እንደ ደነቈራችሁና እንደ ታወራችሁ ቅሩ! ምንም ወይን ጠጅ ሳትጠጡ የሰከራችሁ ሁኑ! ምንም ዐይነት የሚያሰክር መጠጥ ሳትቀምሱ ተንገዳገዱ! 10እግዚአብሔር ከባድ እንቅልፍ ስለ ጣለባችሁ እናንተ ነቢያት ዐይኖቻችሁን ጨፍናችኋል፤ እናንተም ባለ ራእዮች አእምሮአችሁን ዘግታችኋል። #ሮም 11፥8። 11የትንቢት ራእይ ሁሉ ትርጒም ከእናንተ ተሰውሮ እንደ ታሸገ መጽሐፍ ይሆናል፤ ወደሚያነብ ሰው ወስዳችሁ “አንብብልን” ብላችሁ ብትጠይቁት እንኳ “ስለ ታሸገ ላነበው አልችልም” ይላችኋል። 12ማንበብ ወደማይችል ሰው ወስዳችሁ “አንብብልን” ብትሉት፥ “እኔ ማንበብ አልችልም” ይላችኋል።
13ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ይህ ሕዝብ በአፉ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው፤ እኔንም የሚያመልከኝ ሰው ሠራሽ ወግና ሥርዓትን እያስተማረ በከንቱ ነው። #ማቴ. 15፥8-9፤ ማር. 7፥6-7። 14አስደናቂ ተአምርን አከታትዬ በማምጣት ይህ ሕዝብ እንዲገረም አደርገዋለሁ፤ የጥበበኞች ጥበብ ትሰወራለች፤ የአስተዋዮችም ማስተዋል ትረሳለች።” #1ቆሮ. 1፥19።
የወደፊቱ ተስፋ
15ዕቅዳቸውን ከእግዚአብሔር ለመደበቅ ወደ ጥልቅ ቦታ ለሚሄዱ በጨለማ የሠሩትንም ሥራ “ማን ያይብናል? ማን ያውቅብናል?” ለሚሉ ሰዎች ወዮላቸው! 16እናንተ ሁሉን ነገር ትገለባብጣላችሁ። ሸክላ ሠሪው ከሸክላው አይበልጥምን? አንድ የተሠራ ሥራ ሠሪውን “አንተ አልሠራኸኝም” ይለዋልን? ወይስ ደግሞ የሸክላ ዕቃ ሸክላ #ኢሳ. 45፥9። ሠሪውን “ሥራህን አታውቅም” ይለዋልን? 17በጥቂት ጊዜ ውስጥ የሊባኖስ ጫካ የእርሻ ቦታ ይሆናል፤ የእርሻው ቦታ ወደ ጫካነት ይለወጣል።
18ደንቆሮዎች የሚነበብላቸውን መጽሐፍ መስማት የሚችሉበት ጊዜና በጨለማ የሚኖሩ ዕውሮችም ዐይኖቻቸው በርተው የሚያዩበት ጊዜ ይመጣል። 19ትሑታንና ችግረኞች በእስራኤል ቅዱስ በእግዚአብሔር ይደሰታሉ። 20ጨካኞችና ፌዘኞች ይጠፋሉ፤ ክፉ አድራጊዎችም ሁሉ ይደመሰሳሉ። 21ሰውን በነገር ወንጀለኛ የሚያደርጉ፥ ተከሳሽንም በፍርድ ሸንጎ የሚያጠምዱ፥ በሐሰተኛ ምስክር ንጹሕ ሰው ፍትሕ እንዳያገኝ በሐሰት የሚመሰክሩትን ሁሉ እግዚአብሔር ያጠፋቸዋል።
22ስለዚህ አብርሃምን ከችግሩ ያዳነ እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ ይላል፦ “ሕዝቤ ሆይ! ከእንግዲህ ወዲህ ውርደትና ኀፍረት አይደርስባችሁም። 23የእጄ ሥራ የሆኑትን ልጆቻቸውን በመካከላቸው ባዩ ጊዜ ስሜን ይቀድሳሉ፤ የእስራኤልን ቅዱስ ያከብራሉ፤ በእስራኤልም አምላክ ፊት በፍርሃት ይቆማሉ። 24በመንፈስም የሚሳሳቱ ማስተዋልን ይገበያሉ፤ ዘወትር የሚያጒረመርሙ ትምህርትን ይቀበላሉ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 29: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997