የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 13

13
እግዚአብሔር ባቢሎንን እንደሚቀጣ
1የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ እግዚአብሔር ገልጦለት ስለ ባቢሎን የተናገረው የትንቢት ቃል ይህ ነው፤ #ኢሳ. 47፥1-15፤ ኤር. 50፥1—51፥64።
2ምንም ነገር በማይበቅልበት ተራራ ጫፍ ሆናችሁ ምልክት ስጡ፤ ወደ ትዕቢተኞቹ የባቢሎን ገዢዎች ወደሚያስገባው በር እንዲገቡ ትእዛዝ ስጡ። 3ቊጣዬን ተግባራዊ ያደርጉ ዘንድ ቅዱሳኔን አዝዤአለሁ፤ ድሌ የሚያስደስታቸውን ኀያላኔን ጠርቼአለሁ።
4በተራሮች ላይ የሚሰማውን ጩኸት አድምጡ፤ ይህም ጩኸት በአንድነት የተሰበሰቡ የብዙ ሕዝብ መንግሥታት ሁካታ ነው፤ የሠራዊት አምላክ ሠራዊቱን ለጦርነት እያዘጋጀ ነው፤ 5እነርሱም በምድር ዳርቻ ከሚገኙ ከሩቅ አገሮች የመጡ ናቸው፤ እግዚአብሔር አገሪቱን በሞላ ለማጥፋት የቊጣ መሣሪያ የሆነ ሠራዊቱን አሰልፎአል።
6ሁሉን ቻይ እግዚአብሔር ጥፋትን የሚያመጣበት ቀን ስለ ተቃረበ “ዋይ! ዋይ!” እያላችሁ አልቅሱ። #ኢዩ. 1፥15። 7ከፍርሃት የተነሣ የእያንዳንዱ ሰው እጅ ይዝላል፤ የእያንዳንዱም ሰው ልብ በፍርሃት ይዋጣል፥ 8የምትወልድ ሴት በምጥ እንደምትሠቃይ እነርሱም በፍርሃት ይሠቃያሉ፤ እርስ በርሳቸው በፍርሃት ይተያያሉ። 9እነሆ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአል፤ የእግዚአብሔር ቊጣና መዓት የሚፈጸምበት ያ ቀን እጅግ አስፈሪ ነው፤ በዚያን ጊዜ በእርስዋ የሚኖረው ኃጢአተኛ ሕዝብ ስለሚደመሰስ ምድሪቱ ባድማ ትሆናለች። 10እያንዳንዱ ኮከብና የከዋክብት ክምችቱ ብርሃን መስጠቱን ያቆማል፤ የንጋት ፀሐይ ገና ከመውጣትዋ ትጨልማለች፤ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም። #ሕዝ. 32፥7፤ ማቴ. 24፥29፤ ማር. 13፥24-25፤ ሉቃ. 21፥25፤ ራዕ. 6፥12-13።
11እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ዓለምን ስለ ክፋቱ፥ ክፉዎችን ስለ ኃጢአታቸው እቀጣለሁ፤ የኲራተኞችን ማን አለብኝነት አዋርዳለሁ፤ የትዕቢተኛውንም ጭካኔ አጠፋለሁ። 12ሰውን ከወርቅ ይልቅ፥ ከኦፌር ወርቅም የበለጠ ብርቅና ውድ አደርገዋለሁ። 13እኔ የሠራዊት አምላክ ቊጣዬን በምገልጥበት ጊዜ ሰማይን አንቀጠቅጣለሁ፤ ምድርም ከስፍራዋ እንድትናወጥ አደርጋለሁ። #ዘፍ. 19፥24።
14“አዳኝ እንዳባረረው አጋዘንና ጠባቂ እንደሌለው የበግ መንጋ ይባዝን የነበረው እያንዳንዱ ሰው ወደ ወገኖቹ ይመለሳል፤ ወደ አገሩም ይሸሻል። 15የተያዘም ሁሉ በሰይፍ ይገደላል። 16ሕፃኖቻቸው በፊታቸው ተጨፍጭፈው ይሞታሉ፤ ቤቶቻቸው ይዘረፋሉ፤ ሚስቶቻቸው ይደፈራሉ።”
17እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሜዶናውያንን በባቢሎናውያን ላይ አስነሣለሁ፤ እነርሱ ለብር ደንታ የላቸውም፤ በወርቅም አይደለሉም። 18በቀስታቸውና በፍላጻቸው ወጣቶችን ይገድላሉ፤ ሕፃናትን እንኳ አይምሩም፤ ለልጆችም ርኅራኄ የላቸውም። 19የባቢሎን መንግሥት ከመንግሥታት ሁሉ እጅግ የተዋበች ናት፤ ለሕዝብዋም መመኪያ ናት፤ ነገር ግን እኔ እግዚአብሔር ባቢሎንን እንደ ሰዶምና እንደ ገሞራ እገለብጣታለሁ! 20ዳግመኛ የሚኖርባትም አይገኝም፤ የበረሓ ዘላኖች የሆኑ ዐረቦችም ድንኳን አይተክሉባትም፤ እረኞችም መንጋ አያሰማሩባትም። 21የምድረ በዳ አራዊት መፈንጫ ትሆናለች ጒጒቶችም ጎጆ ይሠሩባታል፤ ሰጎኖች በዚያ ይኖራሉ፤ ፍርስራሽዋንም የበረሓ ፍየሎች ይዛለሉበታል። #ኢሳ. 34፥14፤ ሶፎ. 2፥14፤ ራዕ. 18፥2። 22በታላላቅ ሕንጻዎችዋና በቤተ መንግሥትዋ ውስጥ የጅቦችና የተኲላዎች ጩኸት ያስተጋባል፤ እነሆ በዚህ ዐይነት ባቢሎን የምትጠፋበት ጊዜ ደርሶአል።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ