ትንቢተ ኢሳይያስ 14
14
የእስራኤል ሕዝብ ከስደት መመለስ
1እግዚአብሔር ለሕዝቡ ለእስራኤል እንደገና ምሕረትን ያደርጋል፤ የራሱ ወገኖችም አድርጎ ይመርጣቸዋል፤ እንደገናም በአገራቸው እንዲኖሩ ይፈቅድላቸዋል፤ መጻተኞችም እንኳ መጥተው ከእነርሱ ጋር ተስማምተው አብረው ይኖራሉ። 2የብዙ አሕዛብ መንግሥታት የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔር ወደ ሰጣቸው አገር እንዲመለሱ ይረዱአቸዋል፤ አሕዛብ እንደ ባሪያዎች ሆነው የእስራኤልን ሕዝብ ያገለግላሉ፤ ቀድሞ እስራኤልን ማርከው የነበሩ አሁን ደግሞ በእስራኤል እጅ ይማረካሉ፤ ስለዚህም የእስራኤል ሕዝብ ቀድሞ ይጨቊኑአቸው የነበሩትን ሁሉ የመግዛት ሥልጣን ይኖራቸዋል።
የባቢሎን ንጉሥ ወደ ሙታን ዓለም ስለ መውረዱ
3እግዚአብሔር በጭንቀትና በሥቃይ ከምትኖሩበት ከባርነት ኑሮ ነጻ በሚያወጣችሁ ጊዜ 4በባቢሎን ንጉሥ ላይ እንዲህ እያላችሁ ታፌዙበታላችሁ፦
“እነሆ ጨቋኙ ንጉሥ ወደቀ! ከእንግዲህ ወዲህ ማንንም አይጨቊንም! 5እግዚአብሔር የክፉ ገዢዎችን ኀይልና ሥልጣን አስወግዶአል፤ 6እነዚህ ገዢዎች በቊጣቸው ሕዝቦችን ሲጨቊኑ ኖረዋል፤ ያሸነፉአቸውንም ያለማቋረጥ ሲያሠቃዩአቸው ነበር፤ 7በመጨረሻ ግን እነሆ ዓለም ሁሉ የሰላም ዕረፍት ያገኛል፤ ሁሉም በደስታ ይዘምራሉ። 8የሊባኖስ ዛፎችና ዝግባዎች እንኳ ስለ ወደቀው ንጉሥ ደስታቸውን ይገልጣሉ፤ እርሱ ስለ ተወገደ ከእንግዲህ ወዲህ በእነርሱ ላይ መጥረቢያ የሚያነሣባቸው ሰው አይኖርም።
9“የሙታን ዓለም የባቢሎንን ንጉሥ ለመቀበል ተዘጋጅታለች፤ የሙታን መናፍስትም ሁሉ እርሱን ለመቀበል ይንቀሳቀሳሉ፤ በምድር ላይ ኀያላን የነበሩ እጅ ይነሡታል፤ ነገሥታት የነበሩትም ከዙፋናቸው ይነሡለታል። 10እንዲህም ይሉታል፥ ‘አንተም ደግሞ እንደኛ ደካማ ሆንክ! ከእኛም እንደ አንዱ ሆንክ 11ቀድሞ ስለ ክብርህ በመሰንቆ ይዘመርልህ የነበረው ቆመ፤ አሁን አንተ በትዕቢትህ ወደ ሙታን ዓለም ወረድክ። ስለዚህ አልጋህ ምስጥ፥ ልብስህም የትል መንጋ ሆኖአል።’ ”
12አንተ በሚያበራው የአጥቢያ ኮከብ የተመሰልክ የባቢሎን ንጉሥ ሆይ! እንደ ሰማይ ከፍ ካለው ክብርህ እንዴት ወደቅኽ! መንግሥታትን ሁሉ ታዋርድ ነበር፤ አሁን ግን ወደ መሬት ተጣልክ። #ራዕ. 8፥10፤ 9፥1። 13አንተ እንዲህ ብለህ አስበህ ነበር፦ “ወደ ሰማይ ወጥቼ ከእግዚአብሔር ከዋክብት በላይ ዙፋኔን እዘረጋለሁ፤ በስተሰሜን ዳርቻ አማልክት በሚሰበሰቡበት ቦታ በተራራ ላይ እቀመጣለሁ። 14ከደመናዎችም በላይ ወጥቼ በልዑል አምላክ እመሰላለሁ” ብለህ አስበህ ነበር። 15ነገር ግን ወደ ሙታን ዓለም፥ ወደ ጥልቁ ጒድጓድ ወርደሃል። #ማቴ. 11፥23፤ ሉቃ. 10፥15።
16ሙታንም የአንተን ሁኔታ አይተው በመገረም ተመልክተው እንዲህ ይላሉ፦ “ያ ዓለምን ያንቀጠቀጠና መንግሥታትን ያናወጠ ሰው ይህ ነውን? 17ከተሞችን ደምስሶ ዓለምን ወደ ምድረ በዳነት የለወጣት ሰው ይህ ነውን? እስረኞች ነጻ እንዳይለቀቁና ወደ ቤታቸው እንዳይገቡ የሚያደርግ እርሱ አልነበረምን?”
18ነገሥታት ሲሞቱ በክብር ይቀበራሉ። 19አንተ ግን ሳትቀበር በእግር እንደሚረጋገጥ የዛፍ ቅጠል የተጣልክ ሆነሃል፤ ሬሳህም በጦርነት ላይ በሞቱ ሰዎች ሬሳ ተሸፍኖአል፤ ከእነርሱም ሬሳ ጋር በድንጋያማ ጒድጓድ ውስጥ ተጥሎ ተረግጦአል። 20አንተ አገርህን አጥፍተህ፥ የገዛ ሕዝብህን ፈጅተሃል፤ ስለዚህም አንተ እንደ ሌሎች መንግሥታት መቃብር የማግኘት ዕድል አይኖርህም፤ ከክፉ ቤተሰብ መካከል የሚተርፍ ዘር አይኖርም። 21እንግዲህ የልጆቹ መታረድ አሁኑኑ ይዘጋጅ፤ የዚህ ንጉሥ ልጆች በቀድሞ አባቶቻቸው ኃጢአት የሞት ፍርድ ይጠብቃቸዋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ከእነርሱ ማንም ምድርን መውረስም ሆነ ከተሞችን መሥራት አይችልም።
እግዚአብሔር ባቢሎንን እንደሚደመስስ
22የሠራዊት አምላክ እንዲህ ይላል “በባቢሎን ላይ አደጋ ጥዬ አፈራርሳታለሁ፤ ምንም ነገር አላስቀርላትም፤ ለዘር እንኳ የሚተርፍ ትውልድ አይኖራትም፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ። 23ባቢሎንን ረግረግ ስለማደርጋት የአልቅት መፈልፈያ ትሆናለች፤ ባቢሎንን ሁሉን ነገር ጠራርጎ በሚወስድ መጥረጊያ እጠርጋታለሁ፤ እኔ የሠራዊት አምላክ ይህን ተናግሬአለሁ።”
እግዚአብሔር አሦራውያንን እንደሚደመስስ
24የሠራዊት አምላክ እንዲህ ሲል ምሎአል፥ “ያቀድኩት ነገር ሁሉ ተፈጻሚ ይሆናል፤ የወሰንኩትም ነገር ሥራ ላይ ይውላል። #ኢሳ. 10፥5-34፤ ናሆም 1፥1—3፥19፤ ሶፎ. 2፥13-15። 25አሦራውያንን ለእስራኤል በሰጠኋት ምድሬ ላይ እደመስሳቸዋለሁ፤ በተራሮቼም ላይ እረግጣቸዋለሁ፤ ሕዝቤንም ከአሦራውያን የአገዛዝ ቀንበርና ከነበረባቸውም ከባድ ሸክም ነጻ አወጣቸዋለሁ። 26መላውን ዓለም በሚመለከት ያለኝም ዕቅድ ይህ ነው፤ መንግሥታትን ለመቅጣት ክንዴን ዘርግቼአለሁ።” 27የሠራዊት አምላክ ይህን ሁሉ ለማድረግ ወስኖአል፤ ይህ እንዳይሆን የሚያደርግ ማነው? ለመቅጣትም ክንዱን ዘርግቶአል፤ ተከላክሎ ሊያቆመው የሚችልስ ማን ነው?
እግዚአብሔር ፍልስጥኤማውያንን የሚደመስስ መሆኑ
28ንጉሥ አካዝ በሞተበት ዓመት የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው፤ #2ነገ. 16፥20፤ 2ዜ.መ. 18፥27።
29የፍልስጥኤም ሕዝብ ሆይ! እነሆ የተደበደባችሁበት በትር ተሰበረ፤ ሆኖም ደስ ሊላችሁ አይገባም፤ አንድ እባብ በሞተ ጊዜ ሌላ ከእርሱ የባሰ በቦታው ይተካል፤ ከእባብ ዕንቊላል በክንፍ የሚበር እሳት የመሰለ ዘንዶ ይፈለፈላል። 30እጅግ የደኸዩ መጠጊያ ያገኛሉ፤ ድኽነት ያጠቃቸውም ተዝናንተው ይኖራሉ፤ የእናንተን ልጆች ግን በራብ እገድላለሁ፤ የተረፋችሁትንም አጠፋለሁ።
31በመግቢያው በር ሆናችሁ ወዮ በሉ! በከተማው ውስጥ ሆናችሁ ኡኡ! በሉ፤ ከወታደሮቹ አንዱ እንኳ ወደ ኋላ የማይል ኀይለኛ ጠላት ከሰሜን ስለ መጣ ፍልስጥኤማውያን ሁሉ በፍርሃት ይርበድበዱ! #ኤር. 47፥1-7፤ ሕዝ. 25፥15-17፤ ኢዩ. 3፥4-8፤ አሞጽ 1፥6-8፤ ሶፎ. 2፥4-7፤ ዘካ. 9፥5-7።
32ከፍልስጥኤም ለሚመጡ መልእክተኞች የምንሰጠው መልስ ምንድን ነው? እግዚአብሔር ጽዮንን እንደገና መመሥረቱንና በሥቃይ ይኖሩ የነበሩ ሕዝቡ መጠጊያ አግኝተው በሰላም እንዲኖሩ ማድረጉን እንነግራቸዋለን።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 14: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997