ትንቢተ ሆሴዕ 11
11
እግዚአብሔር ለእምቢተኛው ሕዝቡ የሚያሳየው ፍቅር
1እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“ሕዝቤን እስራኤልን ገና በሕፃንነቱ ወደድኩት፤
ልጄን ከግብጽ ጠራሁት። #ዘፀ. 4፥22፤ ማቴ. 2፥15።
2ነገር ግን ሕዝቤን እስራኤልን
ይበልጥ ወደ እኔ እንዲቀርቡ በጠራኋቸው መጠን፥
እነርሱ ይበልጥ ከእኔ እየራቁ ሄዱ።
በዓል ተብሎ ለሚጠራው ጣዖት መሥዋዕት ከማቅረብና
ለምስሎቹም ዕጣን ከማጠን አልተቈጠቡም።
3እጆቻቸውን ይዤ በእግራቸው መረማመድን
ያስተማርኳቸው እኔ ነበርኩ፤
ዕቅፍ አድርጌም ይዤአቸው ነበርኩ፤
እነርሱ ግን እኔ እንደምንከባከባቸው አላወቁም።
4በሰብአዊ ርኅራኄና በፍቅር ትስስር መራኋቸው፤
ቀንበሩን ከጫንቃቸው ላይ በማንሣት
እኔ ራሴ ጐንበስ ብዬ መገብኳቸው።
5“እነርሱ ግን ወደ እኔ መመለስን እምቢ ስላሉ ወደ ግብጽ ይመለሳሉ፤ ለአሦርም ንጉሥ ተገዥዎች ይሆናሉ። 6የጠላት ጦር ከተሞቻቸውን ይመታል፤ የከተሞቻቸውንም በሮች ይሰባብራል፤ ክፉ ምክራቸውንም ያከሽፋል። 7ሕዝቤ ከእኔ መራቅን ፈለጉ፤ ይሁን እንጂ ለእርዳታ ወደ ላይ ይጮኻሉ፤ ግን ማንም ከችግራቸው አያወጣቸውም።
8“እስራኤል ሆይ! እንዴት እተውሃለሁ?
እንዴትስ አሳልፌ እሰጥሃለሁ?
በአዳማና በጸቦይም ያደረግኹትንስ፥
እንዴት አደርግብሃለሁ?
ለአንተ ያለኝ ፍቅር ታላቅ ስለ ሆነ፥
ይህን ሁሉ ላደርግብህ አልፈቅድም! #ዘዳ. 29፥23።
9እኔ በመካከላችሁ የምገኝ ቅዱሱ
አምላክ ነኝ እንጂ ሰው አይደለሁም።
ስለዚህ የቊጣዬን መቅሠፍት አላመጣም፤
ዳግመኛም እስራኤልን አላጠፋም፤
በቊጣዬም ወደ እናንተ አልመጣም።
10“እኔ እግዚአብሔር እነርሱን ለማዳን እንደሚያገሣ አንበሳ ድምፄን ሳሰማ እነርሱ ይከተሉኛል፤ ልጆቼም እየተንቀጠቀጡ ከወደ ምዕራብ ይመጣሉ። 11እንደ ወፍ ከግብጽ፥ እንደ ርግብም ከአሦር እየበረሩ ይመጣሉ፤ ወደ መኖሪያቸው እመልሳቸዋለሁ፤ ይህን የምናገር እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነኝ።”
እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ መፍረዱ
12እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የእስራኤል ሕዝብ በሐሰትና በማታለል ከበውኛል፤ ይሁዳ ግን አሁንም እኔ በእግዚአብሔር በምመራው መንገድ ይሄዳል፤ ለእኔ ለቅዱሱም ታማኝ ነው።
Currently Selected:
ትንቢተ ሆሴዕ 11: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997