ትንቢተ ሆሴዕ 10
10
1የእስራኤል ሕዝብ ብዙ ዘለላ እንደ ያዘ የወይን ተክል ናቸው፤ ፍሬ በበዛላቸው መጠን ብዙ የጣዖት መሠዊያዎችን ሠሩ፤ ምድራቸው ፍሬያማ ሆና በበለጸገችላቸው መጠን የጣዖት መስገጃ ዐምዶችን አስጊጠው ሠሩ። 2ልባቸው በተንኰል የተሞላ ነው፤ የበደላቸውንም ዋጋ ያገኛሉ፤ እግዚአብሔር መሠዊያዎቻቸውን ሁሉ ይሰባብራል፤ የጣዖት መስገጃ ዐምዶቻቸውንም ያፈራርሳል።
3ሕዝቡ “እግዚአብሔርን መፍራት ስለ ተውን ንጉሥ አጥተናል፤ ንጉሥ ቢኖረንስ ምን ያደርግልናል?” ይላሉ። 4በሐሰት መሐላ ቃል ኪዳን በመግባት ከንቱ ንግግር ይናገራሉ፤ ስለዚህ በእርሻ መሬት ውስጥ መርዘኛ አረም እንደሚበቅል በእነርሱም መካከል ክርክር ይስፋፋል።
5በሰማርያ ከተማ የሚኖሩ ሕዝቦች በቤትአዌን ስላለው በጥጃ ምስል በተሠራ ጣዖት በታላቅ ፍርሀት ይርበደበዳሉ፤ ክብሩ ስለ ተገፈፈ ሕዝቡ ያለቅሳሉ፤ የጣዖቱ ካህናትም እሪ ብለው ይጮኻሉ። 6ጣዖቱ ወደ አሦር በመወሰድ ለታላቁ ንጉሥ እጅ መንሻ ሆኖ ይቀርባል፤ እስራኤል ከተከተለው ክፉ ምክር የተነሣ ኀፍረትና ውርደት ይደርስበታል። 7የሰማርያ ንጉሥ የውሃ ላይ ዐረፋ ሆኖ ይቀራል። 8የእስራኤል ሕዝብ አዌን በተባለ ከተማ ጣዖት በማምለክ ኃጢአት የሚሠሩባቸው ከፍተኛ ቦታዎች ይፈራርሳሉ፤ በመሠዊያዎቻቸውም ላይ እሾኽና አሜከላ ይበቅሉባቸዋል፤ በዚያን ጊዜ ሕዝቡ ተራራዎችን “ደብቁን!” ኮረብቶችንም “ጋርዱን!” ይላሉ። #ሉቃ. 23፥30፤ ራዕ. 6፥16።
እግዚአብሔር እስራኤልን እንደሚቀጣ
9እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የእስራኤል ሕዝብ በጊብዓ ኃጢአት ከሠሩበት ጊዜ አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ እኔን ከማሳዘን አልተቈጠቡም፤ ስለዚህ በገባዖን ጦርነት ይነሣባቸዋል። #መሳ. 19፥1-30። 10እነዚህን ዐመፀኞች እቀጣቸዋለሁ፤ አሕዛብ ሁሉ ተሰብስበው በእነርሱ ላይ ይነሣሉ፤ ስለ ድርብ ኃጢአታቸውም ቅጣት ይደርስባቸዋል።
11“እስራኤል ማበራየት እንደምትወድ ጊደር ነበረች፤ ነገር ግን በተዋበ ጫንቃዋ ላይ ቀንበር እጭንበታለሁ፤ በዚህ ዐይነት ይሁዳ ያርሳል፤ የያዕቆብ ልጆች በሙሉ ተጠምደው መሬቱን ያለሰልሳሉ፤ 12እኔም ‘እንግዲህ ዕዳሪውን መሬት ዕረሱ፤ ጽድቅን ለራሳችሁ ዝሩ፤ የማይለዋወጥ ፍቅርን ሰብስቡ፤ እነሆ ወደ እኔ ወደ አምላካችሁ የምትመለሱበት ጊዜ አሁን ነው! እኔም መጥቼ ፍትሕን አሰፍንላችኋለሁ’ አልኩ። #ኤር. 4፥3።
13“እናንተ ግን በራሳችሁ ኀይልና በጀግኖቻችሁ ብዛት በመተማመናችሁ፥ ክፋትን ዘርታችሁ ግፍን ሰበሰባችሁ፤ ሐሰታችሁ ያስገኘውን ፍሬ በላችሁ። 14በሕዝባችሁ ላይ ከባድ ጦርነት ይመጣል፤ ምሽጎቻችሁ ሁሉ ይፈራርሳሉ፤ ይህም ንጉሥ ሸልማን የቤትአርቤልን ከተማ በጦርነት እንዳፈራረሰና እናቶችን ከልጆቻቸው ጋር በምድር ላይ ፈጥፍጦ እንደ ጨረሰበት ጊዜ ይሆናል። 15የቤትኤል ከተማ ነዋሪዎች ሆይ! በሠራችሁት ከባድ ኃጢአት ምክንያት በእናንተም ላይ ይህንኑ የመሰለ ጥፋት ይደርስባችኋል፤ ጦርነቱም እንደ ተነሣ ጎሕ ሲቀድ የእስራኤል ንጉሥ ወዲያውኑ ይገደላል።”
Currently Selected:
ትንቢተ ሆሴዕ 10: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997