ትንቢተ ሆሴዕ 9
9
ሆሴዕ በእስራኤል ላይ ቅጣት እንደሚመጣ መናገሩ
1የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! በየዐውድማው የሚገኘውን የዝሙት ዋጋ ከበዓል የሚሰጥ በረከት መስሎአችሁ፥ ትወዱታላችሁ፤ ይህን በማድረጋችሁ ለአምላካችሁ ታማኞች ሆናችሁ አልተገኛችሁም፤ ስለዚህ እንደ ሌሎች ሕዝቦች መደሰታችሁንና ሐሴት ማድረጋችሁን ተዉ! 2ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ከዐውድማችሁ እህልን፥ ከመጭመቂያችሁም የወይን ጠጅን ከቶ አታገኙም፤ አዲስ የወይን ጠጅም አይገኝም። 3የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔር በሰጣቸው ምድር አይኖሩም፤ ነገር ግን ተገደው ወደ ግብጽ ይመለሳሉ፤ ወደ አሦርም ሄደው በሥርዓት ንጹሕ ያልሆነ ምግብ ይበላሉ። 4በዚያም ለእግዚአብሔር የወይን ጠጅ መባ ማቅረብ አይችሉም፤ መሥዋዕታቸውም እግዚአብሔርን አያስደስትም፤ የእነርሱ እንጀራ ሲርባቸው የሚበሉት እንጂ ወደ እግዚአብሔር ቤት መሥዋዕት ሆኖ የሚቀርብ አይደለም፤ ስለዚህ ለእነርሱ የእዝን እንጀራ ይሆናል፤ እርሱንም የሚመገብ ሁሉ ይረክሳል። 5እንግዲህ ለእግዚአብሔር ክብር በተወሰኑት የዓመት በዓላት ምን ታደርጋላችሁ? 6እነሆ ከጥፋት ለማምለጥ ሲሸሹ ግብጽ ትሰበስባቸዋለች፤ ሜምፊስ ትቀብራቸዋለች፤ ያከማቹት የብር ሀብት ሁሉ ሳማ ለብሶ ይቀራል፤ መኖሪያቸውም እሾኽ ይበቅልበታል።
7የቅጣት ቀን ደርሶአል፤ እስራኤላውያንም የበቀል ቀን መቃረቡን ይወቁ፤ በእናንተ በደልና ጥላቻ ምክንያት ነቢይን እንደ ሞኝ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያደረበትን ሰው እንደ ዕብድ ትቈጥሩታላችሁ። #ሉቃ. 21፥22። 8እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ ነቢዩ ጠባቂ እንዲሆን አድርጎታል፤ ሆኖም በመንገዱ ሁሉ ወጥመድ ተዘርግቶበታል፤ በአምላኩም ቤተ መቅደስ ጥላቻ ይጠብቀዋል። 9የእስራኤል ሕዝብ በገባዖን ዘመን እንደ ነበሩት ሰዎች በጣም ረክሰዋል፤ እግዚአብሔርም በደላቸውን አስቦ ስለ ኃጢአታቸው ይቀጣቸዋል። #መሳ. 19፥1-30።
የእስራኤል ሕዝብ ኃጢአትና ያስከተለው ውድቀት
10እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እስራኤልን ባገኘሁ ጊዜ የወይን ዘለላን ከምድረ በዳ እንደ ማግኘት ነበር፤ የቀድሞ አባቶቻችሁን ባየሁ ጊዜ ቀድሞ የጐመራውን የበለስ ፍሬ እንደማየት ነበር፤ ወደ በዓል ጴዖር በደረሱ ጊዜ ግን ራሳቸውን ለዚያ አሳፋሪ ጣዖት ለይተው አቀረቡ፤ እነርሱም እንደዚያ እንደሚወዱት ጣዖት የረከሱ ሆኑ። #ዘኍ. 25፥1-5። 11የእስራኤል ሕዝብ ታላቅነት እንደ ወፍ በሮ ይጠፋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ መፅነስ የለም፤ ማርገዝ የለም፤ መውለድም የለም። 12ልጆች ወልደው ቢያሳድጉም ሁሉንም ስለምቀሥፋቸው ልጅ አልባ ሆነው ይቀራሉ፤ እኔ ከእነርሱ በራቅሁ ጊዜ ወዮላቸው!”
13እስራኤልን በመልካም መሬት ላይ እንደ ተተከለች የዘንባባ ዛፍ ሆና አየኋት፤ እስራኤላውያን ግን ልጆቻቸውን ለዕርድ አቀረቡ። 14ጌታ ሆይ! ለዚህ ሕዝብ ምን ትሰጠው፤ የሚጨነግፍ ማሕፀንና ደረቅ ጡት ስጣቸው!
የእግዚአብሔር ፍርድ በእስራኤል ላይ
15እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ገና በጌልገላ ሳሉ ክፉ ሥራቸው ተገለጠ፤ እኔም በዚያ የእነርሱን ሥራ መጥላት ጀመርኩ፤ ስለ ሠሩትም ክፉ ሥራ ከሰጠኋቸው ምድር አስወጣቸዋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲያ ለእነርሱ ፍቅር አላሳያቸውም፤ መሪዎቻቸው ሁሉ ዐመፀኞች ሆነዋል። 16የእስራኤል ሕዝብ ነፋስ እንደ መታው፥ ሥሩ እንደ ደረቀና ማፍራት እንደማይችል ዛፍ ያለ ፍሬ ይቀራሉ፤ ልጆች ቢወልዱም እጅግ የሚወዱአቸውን ልጆቻቸውን እገድላለሁ።”
ነቢዩ ስለ እስራኤል የተናገረው የትንቢት ቃል
17እርሱን ስላልታዘዙ አምላኬ ይጥላቸዋል፤ እነርሱም በአሕዛብ መካከል በመንከራተት ይኖራሉ።
Currently Selected:
ትንቢተ ሆሴዕ 9: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997