ወደ ዕብራውያን የተላከ መልእክት 9:11-22

ወደ ዕብራውያን የተላከ መልእክት 9:11-22 አማ05

ነገር ግን ክርስቶስ በመምጣት ላይ ላሉት መልካም ነገሮች የካህናት አለቃ ሆኖ ተገልጦአል፤ እርሱ የገባባት ድንኳን ትልቅና ፍጹም ናት፤ ይህች ድንኳን በሰው እጅ ያልተሠራችና ከዚህ ፍጥረት ያልሆነች ናት። እርሱ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን አንዴ በማያዳግም ሁኔታ የራሱን ደም ይዞ ገባ እንጂ የፍየሎችንና የወይፈኖችን ደም ይዞ አልገባም፤ በዚህም ዐይነት የዘለዓለም ቤዛን አስገኘልን። የፍየሎችና የወይፈኖች ደምና ለመሥዋዕት የተቃጠለች ጊደር ዐመድ በረከሱ ሰዎች ላይ ሲረጭ ከሥጋዊ ርኲሰት አንጽቶ የሚቀድሳቸው ከሆነ፥ በዘለዓለም መንፈስ አማካይነት ራሱን ነውር የሌለበት መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ያቀረበው የክርስቶስ ደም ሕያው እግዚአብሔርን እንድናገለግል ኅሊናችንን ከሞተ ሥራ እንዴት ይበልጥ ያነጻ ይሆን! እነዚያ የተጠሩት እግዚአብሔር በተስፋ የሰጠውን ዘለዓለማዊ ርስት እንዲቀበሉ ክርስቶስ የአዲስ ኪዳን ማእከላዊ አስማሚ ሆኖአል፤ ይህም የሆነው ሰዎችን በመጀመሪያው ቃል ኪዳን ሥር ሆነው ከሠሩት ኃጢአት ለማዳን እርሱ በመሞቱ ነው። ኑዛዜ ሲኖር የተናዛዡን ሞት ማረጋገጥ ያስፈልጋል፤ የኑዛዜ ቃል የሚጸናው ተናዛዡ ከሞተ በኋላ ነው፤ ተናዛዡ በሕይወት ካለ ግን የኑዛዜው ቃል ዋጋ አይኖረውም። በዚህ ምክንያት የመጀመሪያው ኪዳን እንኳ ያለ ደም የጸና አይደለም። በመጀመሪያ ሙሴ የሕጉን ትእዛዞች ለሕዝቡ ሁሉ ነገረ፤ ከዚህ በኋላ የወይፈኖችንና የፍየሎችን ደም ከውሃ ጋር አድርጎ የሕጉን መጽሐፍና ሕዝቡን ሁሉ በሂሶጵና በቀይ የበግ ጠጒር ረጨ፤ የረጨውም “እግዚአብሔር ያዘዛችሁ የቃል ኪዳን ደም ይህ ነው” ብሎ ነው። እንዲሁም በድንኳኒቱና በመገልገያ ዕቃ ሁሉ ላይ ደምን ረጨ። በእርግጥም በሙሴ ሕግ መሠረት ከጥቂት ነገር በቀር ሁሉም ነገር በደም ይነጻል፤ ደም ካልፈሰሰም የኃጢአት ስርየት አይገኝም።