ዕብራውያን 9:11-22

ዕብራውያን 9:11-22 NASV

ክርስቶስ አሁን ስላሉት መልካም ነገሮች ሊቀ ካህናት ሆኖ በመጣ ጊዜ፣ በሰው እጅ ወዳልተሠራችው፣ ከዚህ ፍጥረት ወዳልሆነችው ታላቅና ፍጹም ድንኳን ገባ። የገባውም የፍየልንና የጥጃዎችን ደም ይዞ አይደለም፤ ነገር ግን የዘላለም ቤዛነት ሊያስገኝ የራሱን ደም ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ገባ። የውጭ አካላቸው ይነጻ ዘንድ በረከሱ ሰዎች ላይ የሚረጨው የፍየሎችና የኰርማዎች ደም እንዲሁም የፍየሎችና የጊደር ዐመድ የሚቀድሳቸው ከሆነ፣ በዘላለም መንፈስ አማካይነት ራሱን ነውር አልባ መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ያቀረበው የክርስቶስ ደም፣ ሕያው እግዚአብሔርን እንድናመልክ ኅሊናችንን ከምውት ሥራ እንዴት ይበልጥ ያነጻ ይሆን! ስለዚህም የተጠሩት፣ ተስፋ የተሰጠውን የዘላለም ርስት እንዲቀበሉ ክርስቶስ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው፤ በመጀመሪያው ኪዳን ሥር በነበሩበት ጊዜ ከሠሩት ኀጢአት ነጻ ለማውጣት ቤዛ ሆኖ ሞቷልና። ኑዛዜ በሚኖርበት ጊዜ የተናዛዡን ሞት ማረጋገጥ ግድ ነው፤ ምክንያቱም ኑዛዜው የሚጸናው ሰውየው ሲሞት ብቻ ነው፤ ነገር ግን ተናዛዡ በሕይወት እስካለ ድረስ ኑዛዜው ዋጋ አይኖረውም። ስለዚህ የመጀመሪያው ኪዳን እንኳ ያለ ደም የጸና አልነበረም። ሙሴ እያንዳንዱን የሕግ ትእዛዝ ለሕዝቡ ሁሉ ከተናገረ በኋላ የጥጆችን ደም ከውሃ፣ ከቀይ የበግ ጠጕርና ከሂሶጵ ጋራ ወስዶ፣ በመጽሐፉና በሕዝቡ ላይ ረጨው፤ እንዲህም አለ፤ “እንድትጠብቁት እግዚአብሔር ያዘዛችሁ የኪዳኑ ደም ይህ ነው።” እንዲሁም ድንኳኒቱንና ማገልገያ ዕቃውን ሁሉ በደም ረጨው። በርግጥ ከጥቂት ነገሮች በቀር ሁሉም ነገር በደም መንጻት እንዳለበት ሕጉ ያዝዛል፤ ደም ሳይፈስስ ስርየት የለምና።