ወደ ዕብራውያን የተላከ መልእክት 7:11-28

ወደ ዕብራውያን የተላከ መልእክት 7:11-28 አማ05

እንግዲህ ለሕዝቡ ሕግ የተሰጠው በሌዊ ክህነት መሠረት ነው፤ በዚህ በሌዋውያን ክህነት ፍጹምነት ቢገኝ ኖሮ የአሮን የክህነት ሹመት ሳይሆን የመልከ ጼዴቅ የክህነት ሹመት ያለው ሌላ ካህን መምጣት ባላስፈለገም ነበር፤ የክህነት ሐረጉ ሲለወጥ ሕጉም አብሮ መለወጥ አለበት። ይህ ሁሉ የተነገረለት ካህን ከሌላ ነገድ ነው፤ ከዚህ ነገድ ማንም ወደ መሠዊያው ቀርቦ ያገለገለ የለም። ጌታችን ከይሁዳ ነገድ መሆኑ የታወቀ ነው፤ ሆኖም ሙሴ ስለ ካህናት ሲናገር የይሁዳን ነገድ አስመልክቶ የተናገረው ምንም ነገር የለም። ይህ ነገር በጣም ግልጥ ሆኖ የሚገኘው እንደ መልከጼዴቅ ያለ ሌላ ካህን በሚነሣበት ጊዜ ነው፤ እሱ የክህነት ሹመትን የተቀበለው ለሕይወቱ ፍጻሜ የሌለው በመሆኑ ነው እንጂ ከዘር በመጣ ሥርዓትና ሕግ አይደለም። “እንደ መልከጼዴቅ የክህነት ሹመት አንተ ለዘለዓለም ካህን ነህ” ተብሎ ተመስክሮለታል። የቀድሞው ትእዛዝ ደካማና የማይጠቅም ስለ ሆነ ተሽሮአል በሙሴ ሕግ ምንም ነገር ፍጹም ሊሆን አልቻለም፤ አሁን ግን ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት የተሻለ ተስፋ ተሰጥቶናል። ከዚህም በቀር ይህ ክህነት ያለ እግዚአብሔር መሐላ አልሆነም፤ እነዚያ ከዚህ በፊት ካህናት የሆኑት ያለ መሐላ ነው፤ ኢየሱስ ግን ካህን የሆነው በእግዚአብሔር መሐላ ነው፤ ይህም፦ “እግዚአብሔር ‘አንተ ለዘለዓለም ካህን ነህ’ ብሎ ምሎአል፤ አይለውጥም” ተብሎ በተነገረለት መሠረት ነው። በዚህ መሐላ ምክንያት ኢየሱስ ለተሻለው ቃል ኪዳን ዋስ ሆኖአል። በሞት ምክንያት አንድ ካህን ሳይለወጥ በሥራው ላይ ለዘለዓለም መኖር ስለማይችል የቀድሞዎቹ ካህናት ቊጥራቸው ብዙ ነበር፤ ኢየሱስ ግን ለዘለዓለም የሚኖር በመሆኑ ክህነቱ የማይለወጥ ነው። ስለዚህ እነርሱን ለማማለድ ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ ስለሚኖር በእርሱ አማካይነት ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ሁሉ በፍጹም ሊያድናቸው ይችላል። እንዲህ ያለው ቅዱስ፥ ነቀፋ የሌለበት፥ ንጹሕ፥ ከኃጢአተኞች የተለየ፥ ከሰማይ በላይ ከፍ ያለ የካህናት አለቃ ያስፈልገናል። እርሱ እንደ ሌሎቹ የካህናት አለቆች በመጀመሪያ ስለ ራሱ ኃጢአት፥ በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት በየቀኑ መሥዋዕት ማቅረብ አያስፈልገውም፤ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ባቀረበ ጊዜ ይህን ነገር በማያዳግም ሁኔታ ፈጽሞታል። ሕግ የካህናት አለቆች አድርጎ የሚሾማቸው ደካሞች ሰዎችን ነው፤ ከሕግ በኋላ የመጣው የመሐላ ቃል ግን ለዘለዓለም ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔርን ልጅ ሾሞአል።