ዕብራውያን 7:11-28

ዕብራውያን 7:11-28 NASV

ፍጹምነት የተገኘውና ሕጉ ለሕዝቡ የተሰጠው በሌዊ ክህነት መሠረት ቢሆን ኖሮ፣ እንደ አሮን ሳይሆን እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ያለው ሌላ ካህን መምጣቱ ለምን አስፈለገ? የክህነት ለውጥ ካለ ሕጉም ሊለወጥ ግድ ነውና። ይህ ሁሉ የተነገረለት እርሱ ከሌላ ነገድ ነው፤ ከዚያም ነገድ በመሠዊያ ያገለገለ ማንም የለም። ጌታችን ከይሁዳ ነገድ እንደ መጣ ግልጽ ነውና፤ ሙሴ ስለ ካህናት ሲናገር ይህን ነገድ አስመልክቶ የተናገረው ምንም ነገር የለም። እንደ መልከ ጼዴቅ ያለ ሌላ ካህን ቢነሣ ግን እኛ የተናገርነው ይበልጥ ግልጽ ይሆናል፤ እርሱ ካህን የሆነው በማይጠፋ የሕይወት ኀይል መሠረት እንጂ፣ እንደ ትውልዱ የሕግ ሥርዐት አይደለም፤ እንዲህ ተብሎ ተመስክሮለታል፤ “እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት፣ አንተ ለዘላለም ካህን ነህ።” የቀድሞው ትእዛዝ ደካማና የማይጠቅም በመሆኑ ተሽሯል፤ ሕጉ ማንንም ፍጹም ሊያደርግ ስለማይችል፣ ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት የተሻለ ተስፋ መጥቷል። ይህ ያለ መሐላ አልሆነም። ሌሎች ካህናት የሆኑት ያለ መሐላ ነው፤ እርሱ ግን ካህን የሆነው በመሐላ ነው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናግሮለታል፤ “ጌታ ማለ፤ አሳቡንም አይለውጥም፤ ‘አንተ ለዘላለም ካህን ነህ።’ ” ከዚህ መሐላ የተነሣ፣ ኢየሱስ ለተሻለ ኪዳን ዋስ ሆኗል። በአገልግሎታቸው እንዳይቀጥሉ ሞት ስለ ከለከላቸው፣ የቀድሞዎቹ ካህናት ቍጥራቸው ብዙ ነበር፤ ኢየሱስ ግን ለዘላለም የሚኖር በመሆኑ፣ ክህነቱ የማይሻር ነው። ስለዚህ ስለ እነርሱ እየማለደ ሁልጊዜ በሕይወት ስለሚኖር፣ በርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል። እንግዲህ ለእኛ የሚያስፈልገን፣ ቅዱስ፣ ነቀፋ የሌለበት፣ ንጹሕ፣ ከኀጢአተኞች የተለየና ከሰማያት በላይ የከበረ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ነው። እርሱም እንደ ሌሎቹ ሊቃነ ካህናት መጀመሪያ ስለ ራሱ ኀጢአት፣ ከዚያም ስለ ሕዝቡ ኀጢአት በየቀኑ መሥዋዕት ማቅረብ አያስፈልገውም፤ ራሱን በሰጠ ጊዜ፣ ስለ ኀጢአታቸው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መሥዋዕት አቅርቧልና። ሕጉ ደካማ የሆኑትን ሰዎች ሊቃነ ካህናት አድርጎ ይሾማልና፤ ከሕግ በኋላ የመጣው መሐላ ግን ለዘላለም ፍጹም የሆነውን ልጅ ሾሟል።