ሕግ ወደ ፊት ለሚመጣው መልካም ነገር ምሳሌ (ጥላ) ነበር እንጂ እውነተኛ መልኩ አልነበረም፤ ስለዚህ በየዓመቱ ዘወትር የሚሠዉትን መሥዋዕቶች ይዘው ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡትን ሰዎች ፍጹሞች ሊያደርጋቸው ከቶ አይችልም። ሕጉ ፍጹሞች ሊያደርጋቸው ቢችል ኖሮ ለአምልኮ የሚቀርቡት ሰዎች በማያዳግም ሁኔታ ከኃጢአት ስለ ነጹና ኃጢአት እንደሌለባቸውም በኅሊናቸው ስለሚታወቃቸው መሥዋዕትን ማቅረብ በተዉ ነበር። እነዚያ መሥዋዕቶች ግን በየዓመቱ ኃጢአትን የሚያስታውሱባቸው ናቸው። የወይፈኖችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን ማስወገድ አይችልም። ስለዚህ ክርስቶስ ወደ ዓለም በመጣ ጊዜ እንዲህ አለ፤ “መሥዋዕትንና መባን አልፈለግህም፤ ሰውነትን ግን አዘጋጀህልኝ፤ በሚቃጠል መሥዋዕትና ስለ ኃጢአት ስርየት በሚሠዋ መሥዋዕት አልተደሰትክም፤ በዚያን ጊዜ እኔ፥ ‘አምላኬ ሆይ፥ በመጽሐፍ ስለ እኔ እንደ ተጻፈ ፈቃድህን ለመፈጸም መጥቻለሁ’ ” አልኩ። እሱም በመጀመሪያ እነዚያ በሕጉ መሠረት የታወጁ ቢሆኑ እንኳ “መሥዋዕትንና መባን፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ስለ ኃጢአት ስርየት የሚሠዋውን መሥዋዕት አልፈለግህም፤ በእነርሱም አልተደሰትህም” አለ፤ ቀጥሎም “እነሆ፥ እኔ ፈቃድህን ለመፈጸም መጥቻለሁ” አለ፤ በዚህ ሁኔታ ሁለተኛውን ዐይነት መሥዋዕት በቦታው ለመተካት የመጀመሪያውን ዐይነት መሥዋዕት ሽሮአል። በዚህም “ፈቃድ” በሚለው ቃል መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ አንዴ በማያዳግም ሁኔታ መሥዋዕት ሆኖ በመቅረቡ ምክንያት ተቀድሰናል። እያንዳንዱ ካህን ኃጢአትን ማስወገድ የማይችሉትን እነዚያን መሥዋዕቶች ዘወትር እያቀረበ በየቀኑ ቆሞ ያገለግላል። ክርስቶስ ግን ለሁልጊዜ የሚሆነውን አንዱን መሥዋዕት ካቀረበ በኋላ በእግዚአብሔር አብ ቀኝ ተቀምጦአል። ከእንግዲህ ወዲህ ጠላቶቹ በሥልጣኑ ሥር እስኪሆኑ ድረስ ይጠባበቃል፤ ይህም የሆነው እነዚያን የተቀደሱትን በአንዱ መሥዋዕት አማካይነት ለዘለዓለም ፍጹሞች ስለ አደረጋቸው ነው። መንፈስ ቅዱስም በዚህ ነገር ይመሰክርልናል፤ በመጀመሪያ፥ “ከእነዚያ ቀኖች በኋላ ከእነርሱ ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነው ይላል ጌታ፤ ሕጌን በልባቸው አኖራለሁ፤ በአእምሮአቸውም እጽፈዋለሁ።” ቀጥሎም “ኃጢአታቸውንና ክፉ ሥራቸውን ከእንግዲህ ወዲህ አላስታውስባቸውም” ይላል። ስለዚህ ኃጢአት ሁሉ ከተደመሰሰ በኋላ ስለ ኃጢአት ስርየት የሚቀርብ መሥዋዕት ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።
ወደ ዕብራውያን የተላከ መልእክት 10 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ወደ ዕብራውያን የተላከ መልእክት 10:1-18
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos