ዕብራውያን 10:1-18
ዕብራውያን 10:1-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሕጉ ሊመጣ ያለው የበጎ ነገር እውነተኛ አምሳል ሳይሆን የነገር ጥላ አለውና፤ ስለዚህም በየዓመቱ ዘወትር በሚያቀርቡት በዚያ መሥዋዕት የሚቀርቡትን ሊፈጽም ከቶ አይችልም። ይህስ ባይሆን ከሚሠዉት መሥዋዕት ባረፉ ነበር፥ ለሚሠዉት ኀጢአታቸውን ያስተሰርይላቸው ነበርና፥ ባአንድ ጊዜም ያነጻቸው ነበርና። ነገር ግን በዚያው መሥዋዕት በየዓመቱ የኀጢአት መታሰቢያ አድርገው የሚያቀርቡት ነበራቸው። የላምና የፍየል ደም ኀጢአትን ሊያስተሰርይ አይችልምና። ስለዚህም ወደ ዓለም በሚመጣበት ጊዜ እንዲህ አለ፥ “መሥዋዕትንና ቍርባንን አልወደድህም፤ ሥጋን አለበስኸኝ እንጂ። በሚቃጠል መሥዋዕትና ስለ ኀጢአት በሚቀርበው መሥዋዕት ደስ አላለህም። ያንጊዜ እነሆ፥ በመጽሐፍ ራስ ስለ እኔ እንደ ተጻፈ፥ አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን አደርግ ዘንድ መጥቻለሁ አልሁ።” በዚህ ላይ “መሥዋዕትንና መባን፥ በሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕትንም፥ ስለ ኀጢአትም የሚሠዋ መሥዋዕትን አልወደድህም፤ በእርሱም ደስ አላለህም” ብሎ ተናገረ፤ እነዚህም እንደ ሕግ የሚቀርቡ ናቸው። ከዚህ በኋላ፥ “አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን አደርግ ዘንድ እነሆ፥ መጣሁ” አለ፤ ይህ ቃል የኋለኛውን ያቆም ዘንድ የፊተኛውን ያፈርሳል። በፈቃዱም አንድ ጊዜ በተደረገው በኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋዉ ቍርባን ተቀደስን። ሊቀ ካህናትም ሁሉ ዘወትር እያገለገለ ይቆም ነበር፤ ፈጽሞ ኀጢአት ማስተስረይ የማይቻላቸውን እነዚያን መሥዋዕቶች ብቻም ይሠዋ ነበር። እርሱ ግን ስለ ኀጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘለዓለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ። እንግዲህ ጠላቶቹ ከእግሩ በታች እስኪወድቁ ድረስ ይጠብቃል። ለሚቀደሱትም ለዘለዓለም የምትሆን አንዲት መሥዋዕትን ሠዋ። መንፈስ ቅዱስም ምስክራችን ነው። “ከእነዚያ ወራቶች በኋላ የምገባላቸው ኪዳን ይህቺ ናት ይላል እግዚአብሔር፤ ሕጌን በልባቸው አኖረዋለሁ፤ በልቡናቸውም እጽፈዋለሁ ካለ በኋላ። ከእንግዲህ ወዲህ ኀጢአታቸውንና በደላቸውን ደግሜ አላስብባቸውም” ብሏል። እንዲህም ኀጢአት የሚሰረይ ከሆነ፥ እንግዲህ ወዲህ ስለ ኀጢአት መሥዋዕት አያስፈልግም።
ዕብራውያን 10:1-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሕጉ ወደ ፊት ለሚመጡት መልካም ነገሮች ጥላ ነው እንጂ እውነተኛው አካል አይደለም፤ ስለዚህም በየዓመቱ ዘወትር ያለ ማቋረጥ የሚቀርበው ተደጋጋሚ መሥዋዕት፣ ለአምልኮ የሚቀርቡትን ሰዎች ፍጹም ሊያደርጋቸው ከቶ አይችልም። ፍጹም ሊያደርጋቸው ቢችል ኖሮ፣ መሥዋዕት ማቅረቡን ይተዉት አልነበረምን? ደግሞም ለአምልኮ የሚቀርቡት ሰዎች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለሚነጹ፣ በኅሊናቸው ኀጢአተኝነት ባልተሰማቸውም ነበር። ነገር ግን እነዚህ መሥዋዕቶች በየዓመቱ ኀጢአትን የሚያስታውሱ ናቸው፤ ምክንያቱም የኰርማዎችና የፍየሎች ደም ኀጢአትን ማስወገድ አይችልም። ስለዚህ ክርስቶስ ወደ ዓለም በመጣ ጊዜ እንዲህ ብሏል፤ “መሥዋዕትንና መባን አልፈለግህም፤ ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ፤ በሚቃጠል መሥዋዕትና ለኀጢአት በሚቀርብ መሥዋዕት ደስ አልተሰኘህም። በዚያን ጊዜ እንዲህ አልሁ፤ ‘ስለ እኔ በመጽሐፍ እንደ ተጻፈ፣ አምላክ ሆይ፤ እነሆኝ፤ ፈቃድህን ለማድረግ መጥቻለሁ።’ ” ሕጉ ይህ እንዲደረግ ቢያዝም፣ እርሱ ግን በመጀመሪያ፣ “መሥዋዕትንና መባን፣ የሚቃጠል መሥዋዕትንና ስለ ኀጢአት የሚቀርበውን መሥዋዕት አልፈለግህም፤ ደስም አልተሰኘህበትም” ይላል። ቀጥሎም፣ “እነሆኝ፤ ፈቃድህን ለማድረግ መጥቻለሁ” አለ፤ ሁለተኛውን ለመመሥረት የመጀመሪያውን ሻረ። በዚህ ፈቃድ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ አማካይነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በቀረበው መሥዋዕት ተቀድሰናል። ካህን ሁሉ በየዕለቱ ቆሞ አገልግሎቱን ያከናውናል፤ ኀጢአትን ማስወገድ ከቶ የማይችሉትን እነዚያኑ መሥዋዕቶች ዘወትር ያቀርባል። ይህኛው ካህን ግን አንዱን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ፣ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጧል፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጠላቶቹ የእግሩ መረገጫ እስኪሆኑ ድረስ ይጠብቃል፤ ምክንያቱም በአንዱ መሥዋዕት እነዚያን የሚቀደሱትን ለዘላለም ፍጹማን አድርጓቸዋል። መንፈስ ቅዱስም ስለዚህ ነገር ይመሰክርልናል፤ በመጀመሪያ እንዲህ ይላል፤ “ከዚያም በኋላ ከእነርሱ ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው፤ ይላል ጌታ፤ ሕጌን በልባቸው አኖራለሁ፤ በአእምሯቸውም እጽፈዋለሁ።” ደግሞም፣ “ኀጢአታቸውንና ዐመፃቸውን፣ ከእንግዲህ አላስብም” ይላል። እነዚህ ይቅር ከተባሉ በኋላ ከእንግዲህ ስለ ኀጢአት የሚቀርብ መሥዋዕት አይኖርም።
ዕብራውያን 10:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሕጉ ሊመጣ ያለው የበጎ ነገር እውነተኛ አምሳል ሳይሆን የነገር ጥላ አለውና፥ ስለዚህም በየዓመቱ ዘወትር በሚያቀርቡት በዚያ መሥዋዕት የሚቀርቡትን ሊፈጽም ከቶ አይችልም። እንደዚህማ ባይሆን፥ የሚያመልኩት አንድ ጊዜ ነጽተው ከዚያ በኋላ በሕሊናቸው ኃጢአትን ስላላወቁ ማቅረብን በተዉ አልነበረምን? ነገር ግን በዚያ መሥዋዕት በየዓመቱ የኃጢአት መታሰቢያ አለ፤ የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን እንዲያስወግድ የማይቻል ነውና። ስለዚህ ወደ ዓለም ሲገባ፦ መሥዋዕትንና መባን አልወደድህም ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ፤ በሙሉ በሚቃጠል መሥዋዕትና ሰለ ኃጢአት በሚሰዋ መሥዋዕት ደስ አላለህም። በዚያን ጊዜ፦ እነሆ፥ በመጽሐፍ ጥቅልል ስለ እኔ እንደ ተጻፈ፥ አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ አልሁ ይላል። በዚህ ላይ፦ መሥዋዕትንና መባን በሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕትንም ስለ ኃጢአትም የሚሰዋ መሥዋዕትን አልወደድህም በእርሱም ደስ አላለህም ብሎ፥ እነዚህም እንደ ሕግ የሚቀርቡት ናቸው፥ ቀጥሎ፦ እነሆ፥ አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ ብሎአል። ሁለተኛውንም ሊያቆም የፊተኛውን ይሽራል። በዚህም ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ አንድ ጊዜ ፈጽሞ በማቅረብ ተቀድሰናል። ሊቀ ካህናትም ሁሉ ዕለት ዕለት እያገለገለ ኃጢአትን ሊያስወግዱ ከቶ የማይችሉትን እነዚያን መሥዋዕቶች ብዙ ጊዜ እያቀረበ ቆሞአል፤ እርሱ ግን ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ፥ ጠላቶቹም የእግሩ መረገጫ እስኪደረጉ ድረስ ወደ ፊት ይጠብቃል። አንድ ጊዜ በማቅረብ የሚቀደሱትን የዘላለም ፍጹማን አድርጎአቸዋልና። መንፈስ ቅዱስም ደግሞ ስለዚህ ይመሰክርልናል፤ ከዚያ ወራት በኋላ ከእነርሱ ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው ይላል ጌታ፤ በልባቸው ሕጌን አኖራለሁ በልቡናቸውም እጽፈዋለሁ ብሎ ከተናገረ በኋላ፥ ኃጢአታቸውንና ዓመጻቸውንም ደግሜ አላስብም ይላል። የእነዚህም ስርየት ባለበት ዘንድ፥ ከዚህ ወዲህ ስለ ኃጢአት ማቅረብ የለም።
ዕብራውያን 10:1-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሕግ ወደ ፊት ለሚመጣው መልካም ነገር ምሳሌ (ጥላ) ነበር እንጂ እውነተኛ መልኩ አልነበረም፤ ስለዚህ በየዓመቱ ዘወትር የሚሠዉትን መሥዋዕቶች ይዘው ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡትን ሰዎች ፍጹሞች ሊያደርጋቸው ከቶ አይችልም። ሕጉ ፍጹሞች ሊያደርጋቸው ቢችል ኖሮ ለአምልኮ የሚቀርቡት ሰዎች በማያዳግም ሁኔታ ከኃጢአት ስለ ነጹና ኃጢአት እንደሌለባቸውም በኅሊናቸው ስለሚታወቃቸው መሥዋዕትን ማቅረብ በተዉ ነበር። እነዚያ መሥዋዕቶች ግን በየዓመቱ ኃጢአትን የሚያስታውሱባቸው ናቸው። የወይፈኖችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን ማስወገድ አይችልም። ስለዚህ ክርስቶስ ወደ ዓለም በመጣ ጊዜ እንዲህ አለ፤ “መሥዋዕትንና መባን አልፈለግህም፤ ሰውነትን ግን አዘጋጀህልኝ፤ በሚቃጠል መሥዋዕትና ስለ ኃጢአት ስርየት በሚሠዋ መሥዋዕት አልተደሰትክም፤ በዚያን ጊዜ እኔ፥ ‘አምላኬ ሆይ፥ በመጽሐፍ ስለ እኔ እንደ ተጻፈ ፈቃድህን ለመፈጸም መጥቻለሁ’ ” አልኩ። እሱም በመጀመሪያ እነዚያ በሕጉ መሠረት የታወጁ ቢሆኑ እንኳ “መሥዋዕትንና መባን፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ስለ ኃጢአት ስርየት የሚሠዋውን መሥዋዕት አልፈለግህም፤ በእነርሱም አልተደሰትህም” አለ፤ ቀጥሎም “እነሆ፥ እኔ ፈቃድህን ለመፈጸም መጥቻለሁ” አለ፤ በዚህ ሁኔታ ሁለተኛውን ዐይነት መሥዋዕት በቦታው ለመተካት የመጀመሪያውን ዐይነት መሥዋዕት ሽሮአል። በዚህም “ፈቃድ” በሚለው ቃል መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ አንዴ በማያዳግም ሁኔታ መሥዋዕት ሆኖ በመቅረቡ ምክንያት ተቀድሰናል። እያንዳንዱ ካህን ኃጢአትን ማስወገድ የማይችሉትን እነዚያን መሥዋዕቶች ዘወትር እያቀረበ በየቀኑ ቆሞ ያገለግላል። ክርስቶስ ግን ለሁልጊዜ የሚሆነውን አንዱን መሥዋዕት ካቀረበ በኋላ በእግዚአብሔር አብ ቀኝ ተቀምጦአል። ከእንግዲህ ወዲህ ጠላቶቹ በሥልጣኑ ሥር እስኪሆኑ ድረስ ይጠባበቃል፤ ይህም የሆነው እነዚያን የተቀደሱትን በአንዱ መሥዋዕት አማካይነት ለዘለዓለም ፍጹሞች ስለ አደረጋቸው ነው። መንፈስ ቅዱስም በዚህ ነገር ይመሰክርልናል፤ በመጀመሪያ፥ “ከእነዚያ ቀኖች በኋላ ከእነርሱ ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነው ይላል ጌታ፤ ሕጌን በልባቸው አኖራለሁ፤ በአእምሮአቸውም እጽፈዋለሁ።” ቀጥሎም “ኃጢአታቸውንና ክፉ ሥራቸውን ከእንግዲህ ወዲህ አላስታውስባቸውም” ይላል። ስለዚህ ኃጢአት ሁሉ ከተደመሰሰ በኋላ ስለ ኃጢአት ስርየት የሚቀርብ መሥዋዕት ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።
ዕብራውያን 10:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሕጉ ወደ ፊት ለሚመጣው መልካም ነገር እውነተኛ አምሳል ሳይሆን ጥላ በመሆኑ፥ እውነተኛ አካል አይደለም። በየዓመቱም ዘወትር በሚያቀርቡት መሥዋዕት የሚቀርቡትን ለፍጽምና ሊያበቃ ከቶ አይችልም። እንደዚህማ ባይሆን፥ የሚያመልኩት አንድ ጊዜ ነጽተው ከዚያ በኋላ በሕሊናቸው ኃጢአትን ስላላወቁ ማቅረብን ባቆሙ አልነበረምን? ነገር ግን በዚያ መሥዋዕት ዓመታዊ የኃጢአት መታሰቢያ ነው ያለው፤ የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን ለማስወገድ አይችልም። በዚህ ምክንያት፥ ወደ ዓለም ሲመጣ፥ “መሥዋዕትንና መባን አልወደድክም፤ ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ፤ በሚቃጠልና ስለ ኃጢአት በሚሠዋ መሥዋዕት፥ አንተ ደስ አላለህም። በዚያን ጊዜ፥ ‘እነሆ በመጽሐፍ ጥቅልል ስለ እኔ እንደ ተጻፈ፥ አምላኬ ሆይ! ፈቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ፥’ አልኩ፤” ይላል። በዚህ ላይ “መሥዋዕትንና መባን የሚቃጠል መሥዋዕትንም፥ ስለ ኃጢአትም የሚሰዋ መሥዋዕትን አልወደድህም፥ በእርሱም ደስ አላለህም፤” ይላል። እነዚህም እንደ ሕጉ የሚቀርቡት ናቸው። ከዚያም “እነሆ፥ ፈቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ፤” ብሎአል። ሁለተኛውንም ሊያቆም የፊተኛውን ይሽራል። በዚህም ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በማቅረብ ተቀድሰናል። ሊቀ ካህናትም ሁሉ በየዕለቱ እያገለገለ እነዚያን ኃጢአትን ሊያስወግዱ ከቶ የማይችሉትን መሥዋዕቶች ደጋግሞ ለማቅረብ ይቆማል፤ እርሱ ግን ስለ ኃጢአት አንድ መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ፤ አሁን ጠላቶቹም የእግሩ መረገጫ እስኪሆኑ ድረስ ወደ ፊት ይጠብቃል። ምክንያቱም አንድ ጊዜ ራሱን መሥዋዕት በማቅረብ የሚቀደሱትን የዘላለም ፍጹማን አድርጎአቸዋል። መንፈስ ቅዱስም ስለዚህ ይመሰክርልናል፤ እንዲህ በማለት፦ “ከነዚያ ወራት በኋላ ከእነርሱ ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው፥ ይላል ጌታ፤ “በልባቸው ሕጌን አኖራለሁ፥ በልቡናቸውም እጽፈዋለሁ፤” እንደዚሁም፥ “ኀጢአታቸውንና ዐመጻቸውንም ደግሜ አላስብም፤” ይላል። የእነዚህም ስርየት ባለበት፥ ከእንግዲህ ወዲህ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ማቅረብ የለም።