የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ወደ ዕብራውያን የተላከ መልእክት 10

10
1ሕግ ወደ ፊት ለሚመጣው መልካም ነገር ምሳሌ (ጥላ) ነበር እንጂ እውነተኛ መልኩ አልነበረም፤ ስለዚህ በየዓመቱ ዘወትር የሚሠዉትን መሥዋዕቶች ይዘው ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡትን ሰዎች ፍጹሞች ሊያደርጋቸው ከቶ አይችልም። 2ሕጉ ፍጹሞች ሊያደርጋቸው ቢችል ኖሮ ለአምልኮ የሚቀርቡት ሰዎች በማያዳግም ሁኔታ ከኃጢአት ስለ ነጹና ኃጢአት እንደሌለባቸውም በኅሊናቸው ስለሚታወቃቸው መሥዋዕትን ማቅረብ በተዉ ነበር። 3እነዚያ መሥዋዕቶች ግን በየዓመቱ ኃጢአትን የሚያስታውሱባቸው ናቸው። 4የወይፈኖችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን ማስወገድ አይችልም።
5ስለዚህ ክርስቶስ ወደ ዓለም በመጣ ጊዜ እንዲህ አለ፤
“መሥዋዕትንና መባን አልፈለግህም፤
ሰውነትን ግን አዘጋጀህልኝ፤ #መዝ. 40፥6-8።
6በሚቃጠል መሥዋዕትና
ስለ ኃጢአት ስርየት በሚሠዋ መሥዋዕት
አልተደሰትክም፤
7በዚያን ጊዜ እኔ፥
‘አምላኬ ሆይ፥ በመጽሐፍ ስለ እኔ እንደ ተጻፈ
ፈቃድህን ለመፈጸም መጥቻለሁ’ ” አልኩ።
8እሱም በመጀመሪያ እነዚያ በሕጉ መሠረት የታወጁ ቢሆኑ እንኳ “መሥዋዕትንና መባን፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ስለ ኃጢአት ስርየት የሚሠዋውን መሥዋዕት አልፈለግህም፤ በእነርሱም አልተደሰትህም” አለ፤ 9ቀጥሎም “እነሆ፥ እኔ ፈቃድህን ለመፈጸም መጥቻለሁ” አለ፤ በዚህ ሁኔታ ሁለተኛውን ዐይነት መሥዋዕት በቦታው ለመተካት የመጀመሪያውን ዐይነት መሥዋዕት ሽሮአል። 10በዚህም “ፈቃድ” በሚለው ቃል መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ አንዴ በማያዳግም ሁኔታ መሥዋዕት ሆኖ በመቅረቡ ምክንያት ተቀድሰናል።
11እያንዳንዱ ካህን ኃጢአትን ማስወገድ የማይችሉትን እነዚያን መሥዋዕቶች ዘወትር እያቀረበ በየቀኑ ቆሞ ያገለግላል። #ዘፀ. 29፥38። 12ክርስቶስ ግን ለሁልጊዜ የሚሆነውን አንዱን መሥዋዕት ካቀረበ በኋላ በእግዚአብሔር አብ ቀኝ ተቀምጦአል። 13ከእንግዲህ ወዲህ ጠላቶቹ በሥልጣኑ ሥር እስኪሆኑ ድረስ ይጠባበቃል፤ #መዝ. 110፥1። 14ይህም የሆነው እነዚያን የተቀደሱትን በአንዱ መሥዋዕት አማካይነት ለዘለዓለም ፍጹሞች ስለ አደረጋቸው ነው።
15መንፈስ ቅዱስም በዚህ ነገር ይመሰክርልናል፤ በመጀመሪያ፥
16“ከእነዚያ ቀኖች በኋላ
ከእነርሱ ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነው ይላል ጌታ፤
ሕጌን በልባቸው አኖራለሁ፤
በአእምሮአቸውም እጽፈዋለሁ።” #ኤር. 31፥33።
17ቀጥሎም “ኃጢአታቸውንና ክፉ ሥራቸውን
ከእንግዲህ ወዲህ አላስታውስባቸውም” ይላል። #ኤር. 31፥34።
18ስለዚህ ኃጢአት ሁሉ ከተደመሰሰ በኋላ ስለ ኃጢአት ስርየት የሚቀርብ መሥዋዕት ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።
ወደ እግዚአብሔር መቅረብ የሚገባ መሆኑ
19እንግዲህ ወንድሞቼ ሆይ! በኢየሱስ ደም አማካይነት ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ለመግባት የሚያስችለንን መተማመኛ አግኝተናል፤ 20የምንገባውም በመጋረጃው፥ ማለትም በሥጋው አማካይነት በከፈተልን በአዲሱና ሕያው በሆነው መንገድ ነው። 21በእግዚአብሔር ቤት ላይ ሥልጣን ያለው ትልቅ ካህን አለን። 22ስለዚህ ከክፉ ኅሊና እንድንነጻ ልባችንን ተረጭተን፥ ሰውነታችንንም በንጹሕ ውሃ ታጥበን፥ ቅን ልብና እውነተኛ እምነት ይዘን ወደ እግዚአብሔር እንቅረብ። #ዘሌ. 8፥30፤ ሕዝ. 36፥25። 23የተስፋውን ቃል የሰጠን ታማኝ ስለ ሆነ አሁን አምነን የምንመሰክረውን ተስፋ ሳናወላውል አጥብቀን እንያዝ። 24በፍቅርና በመልካም ሥራ ነቅተን እንድንኖር አንዱ ሌላውን ያሳስበው፤ 25ዘወትር እየተገናኘን እርስ በርሳችን እንበረታታ እንጂ አንዳንዶች ማድረግ እንደ ለመዱት መሰብሰባችንን አንተው፤ ይልቁንም የጌታ መምጫ ቀን መቃረቡን እያስታወሳችሁ ይህን ነገር በይበልጥ አድርጉ።
26እውነትን ካወቅን በኋላ ሆን ብለን ኃጢአት ብንሠራ ከእንግዲህ ወዲህ ስለ ኃጢአት የሚቀርብ ምንም መሥዋዕት አይኖረንም። 27አሁን የሚቀረው ግን ወደ ፊት የሚሆነው አስፈሪ ፍርድና ተቃዋሚዎችን የሚያቃጥል አስፈሪ እሳት ነው። #ኢሳ. 26፥11። 28የሙሴን ሕግ የጣሰ ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች ከመሰከሩበት ያለ ምሕረት በሞት ይቀጣል። #ዘዳ. 17፥6፤ 19፥15። 29ታዲያ፥ የእግዚአብሔርን ልጅ የናቀ፥ የተቀደሰበትን የቃል ኪዳን ደም ያረከሰ፥ የጸጋን መንፈስ የሰደበ፥ እንዴት ያለ የባሰ ቅጣት የሚገባው ይመስላችኋል! #ዘፀ. 24፥8። 30“በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ተገቢ ዋጋን እከፍላለሁ” ያለው ማን መሆኑን እናውቃለን፤ እንዲሁም “እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ይፈርዳል” ይላል ጌታ። #ዘዳ. 32፥35-36። 31ስለዚህ በሕያው እግዚአብሔር እጅ መውደቅ እጅግ የሚያስፈራ ነው።
32ብርሃን ከበራላችሁ በኋላ ብዙ መከራ ተቀብላችሁ የታገሣችሁባቸውን እነዚያን የቀድሞዎቹን ቀኖች አስታውሱ። 33አንዳንድ ጊዜ በሰው ፊት ተሰድባችኋል፤ ተንገላታችኋል፤ አንዳንድ ጊዜም ይህ ዐይነት ሥቃይ ከደረሰባቸው ሰዎች ጋር ጓደኞች በመሆናችሁ መከራ ተቀብላችኋል። 34እናንተ የተሻለና ነዋሪ ሀብት በሰማይ እንዳላችሁ በማወቃችሁ ለእስረኞች ራራችሁላቸው፤ ንብረታችሁም ሲወሰድባችሁ ታግሣችሁ ሁኔታውን በደስታ ተቀበላችሁ። 35እንግዲህ፥ ታላቅ ሽልማት የምታገኙበትን መተማመኛችሁን አትጣሉት። 36የእግዚአብሔርን ፈቃድ ፈጽማችሁ እግዚአብሔር ሊሰጣችሁ ቃል የገባላችሁን ነገር ለማግኘት በትዕግሥት መጠበቅ ያስፈልጋችኋል። 37ለዚህም እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፤
“ያ የሚመጣው ከጥቂት ጊዜ በኋላ ይመጣል፤
አይዘገይምም፤
38የእኔ የሆነ ጻድቁ ሰው ግን በእምነት ሕይወትን ያገኛል፤
ወደ ኋላው ቢያፈገፍግ ግን እኔ በእርሱ
አልደሰትም።” #ዕን. 2፥3-4።
39እኛ ግን አምነው ከሚድኑት ወገን ነን እንጂ ወደ ኋላ አፈግፍገው ከሚጠፉት ሰዎች ወገን አይደለንም።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ