ወደ ዕብራውያን የተላከ መልእክት 1:1-14

ወደ ዕብራውያን የተላከ መልእክት 1:1-14 አማ05

እግዚአብሔር በቀድሞ ዘመናት በተለያዩ መንገዶች፥ በነቢያት አማካይነት ለአባቶቻችን ብዙ ጊዜ ተናግሮ ነበር፤ አሁን ግን በእነዚህ በኋለኞቹ ዘመናት ሁሉን ነገር ወራሽ ባደረገው በልጁ አማካይነት ለእኛ ተናገረን፤ ዓለምንም ሁሉ የፈጠረው በእርሱ ነው። እርሱ የእግዚአብሔር ክብር ነጸብራቅ ነው፤ እርሱ በባሕርዩ ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም ትክክል ነው። በኀያል ቃሉ ዓለምን ሁሉ ደግፎ ይዞአል፤ ሰዎችንም ከኃጢአት ካነጻ በኋላ በሰማይ በኀያሉ እግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦአል። ለእርሱ የተሰጠው ስም ከመላእክት ስም በላይ እንደ መሆኑ መጠን የእግዚአብሔር ልጅ ከመላእክት እጅግ በጣም የላቀ ነው። እግዚአብሔር ከቶ ከመላእክት መካከል፥ “አንተ ልጄ ነህ፤ ዛሬ ወልጄሃለሁ፤” ወይም “እኔ አባት እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጄ ይሆናል” ያለው ማንን ነው? እግዚአብሔር የበኲር ልጁን ወደ ዓለም በላከ ጊዜ “የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉ ይስገዱለት” ይላል። ስለ መላእክቱ ግን “መላእክቱን መናፍስት፥ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል ያደርጋል” ይላል። ስለ ልጁ ግን፥ “አምላክ ሆይ! ዙፋንህ ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይኖራል፤ መንግሥትህንም በትክክል ታስተዳድራለህ፤ ጽድቅን ወደድህ፤ ዐመፃንም ጠላህ፤ በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር አምላክህ መረጠህ፤ ከጓደኞችህም ይበልጥ ደስታን በሚሰጥ ቅባት ቀባህ” ይላል። እንዲሁም፥ “ጌታ ሆይ! አንተ በመጀመሪያ ምድርን መሠረትህ፤ ሰማያት የእጅህ ሥራ ናቸው፤ እነርሱ ሁሉ ይጠፋሉ፤ አንተ ግን ትኖራለህ፤ እነርሱ ሁሉ እንደ ልብስ ያረጃሉ። እንደ መጐናጸፊያም ትጠቀልላቸዋለህ፤ እነርሱም እንደ ልብስ ይለወጣሉ። አንተ ግን ሁልጊዜ ያው ነህ፤ ለዘመንህም ፍጻሜ የለውም” ይላል። እግዚአብሔር ከመላእክቱ መካከል፥ “ጠላቶችህን ከሥልጣንህ ሥር እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ” ያለው ማንን ነው? ታዲያ፥ መላእክት ሁሉ የሚድኑትን ሰዎች ለማገልገል የሚላኩ የእግዚአብሔር አገልጋዮች የሆኑ መናፍስት አይደሉምን?