ዕብራውያን 1:1-14

ዕብራውያን 1:1-14 NASV

እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ በተለያየ ጊዜና በልዩ ልዩ መንገድ በነቢያት በኩል ለአባቶቻችን ተናግሮ፣ በዚህ መጨረሻ ዘመን ግን ሁሉን ወራሽ ባደረገውና ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ ለእኛ ተናገረን። እርሱ የእግዚአብሔር ክብር ነጸብራቅና የባሕርዩ ትክክለኛ ምሳሌ ሆኖ፣ በኀያል ቃሉ ሁሉን ደግፎ ይዟል። የኀጢአት መንጻት ካስገኘ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ። ስለዚህ የወረሰው ስም ከመላእክት ስም እንደሚበልጥ ሁሉ፣ እርሱም ከመላእክት እጅግ የላቀ ሆኗል። እግዚአብሔር፣ “አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድሁህ፤” ወይስ ደግሞ፣ “እኔ አባት እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጄ ይሆናል” ያለው ከመላእክት ከቶ ለማን ነው? ደግሞም እግዚአብሔር በኵሩን ወደ ዓለም ሲያስገባ፣ “የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉ ይስገዱለት” ይላል። ስለ መላእክትም ሲናገር፣ “መላእክቱን ነፋሳት፣ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል ያደርጋል” ይላል። ስለ ልጁ ግን እንዲህ ይላል፤ “አምላክ ሆይ፤ ዙፋንህ ከዘላለም እስከ ዘላለም ጸንቶ ይኖራል፤ የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ይሆናል። ጽድቅን ወደድህ፤ ዐመፃን ጠላህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ ከባልንጀሮችህ በላይ አስቀመጠህ፣ የደስታንም ዘይት ቀባህ።” ደግሞም እንዲህ ይላል፤ “ጌታ ሆይ፤ አንተ በመጀመሪያ የምድርን መሠረት አኖርህ፤ ሰማያትም የእጆችህ ሥራ ናቸው። እነርሱ ይጠፋሉ፤ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፤ እንደ መጐናጸፊያ ትጠቀልላቸዋለህ፤ እንደ ልብስም ይለወጣሉ። አንተ ግን ያው አንተ ነህ፤ ዘመንህም ፍጻሜ የለውም።” እግዚአብሔር፣ “ጠላቶችህን ለእግርህ መረገጫ እስከማደርግልህ ድረስ፣ በቀኜ ተቀመጥ” ያለው ከመላእክት ከቶ ለማን ነው? መላእክት ሁሉ መዳንን የሚወርሱትን ለማገልገል የሚላኩ አገልጋይ መናፍስት አይደሉምን?