ትንቢተ ሐጌ 2
2
የአዲሱ ቤተ መቅደስ ውበትና ግርማ
1ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፥ ሰባተኛው ወር በገባ በሃያ አንደኛው ቀን በነቢዩ ሐጌ አማካይነት እግዚአብሔር ዳግመኛ ተናገረ፤ 2ጌታ ይሁዳ ገዢ ለሆነው ለሰላትያል ልጅ ለዘሩባቤል፥ ሊቀ ካህናት ለሆነው ለኢዮሴዴቅ ልጅ ለኢያሱና ተርፎ ከስደት ለተመለሰው ሕዝብ እንዲህ ብለህ ተናገር አለው። 3“የዚህ ቤተ መቅደስ የቀድሞ ክብሩ እንዴት እንደ ነበረ ያየ ሰው በእናንተ መካከል አለን? ዛሬስ እንዴት ሆኖ ታዩታላችሁ? ይህ በእናንተ ዘንድ እንደሌለ የሚቈጠር አይደለምን? #ዕዝ. 3፥12። 4አሁን ግን ዘሩባቤል ሆይ! በርታ ሊቀ ካህናቱ የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ ሆይ! በርታ፤ የሀገሪቱ ሕዝብ ሆይ! በርቱ! እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ። እኔ ከእናንተ ጋር እሆናለሁ። 5ከግብጽ ምድር በወጣችሁ ጊዜ ‘እኔ ከእናንተ ጋር እሆናለሁ’ ብዬ በሰጠሁት የተስፋ ቃል መሠረት አሁንም መንፈሴ ከእናንተ ጋር ስለ ሆነ አይዞአችሁ አትፍሩ” ብሎ ነገራቸው። #ዘፀ. 29፥45-46።
6የሠራዊት አምላክ እንዲህ ይላል፦ “በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደገና ሰማይንና ምድርን፥ ባሕርንና የብስን አናውጣለሁ፤ #ዕብ. 12፥26። 7መንግሥታትን ሁሉ እገለብጣለሁ፤ ሀብታቸውንም ሁሉ ወደዚህ እንዲመጣ አደርጋለሁ፤ ስለዚህም ቤተ መቅደሱ በሀብት የተሞላ ይሆናል። 8በዓለም የሚገኝ ወርቅና ብር ሁሉ የእኔ ነው። 9አዲሱ ቤተ መቅደስ ከፊተኛው ይበልጥ የተዋበ ይሆናል፤ እኔም በዚያ ለሕዝቤ የተሟላ ሰላምን እሰጣለሁ፤” የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአል።
ነቢዩ ሐጌ ለካህናት የሰጠው ምክር
10ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ዘጠነኛው ወር በገባ በሃያ አራተኛው ቀን የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በነቢዩ ሐጌ አማካይነት እንዲህ ሲል ተናገረ፤ 11“ካህናቱን ስለ ሕጉ ጠይቃቸው፤ 12ለምሳሌ አንድ ሰው የተቀደሰ ሥጋ ከመሠዊያ ላይ ወስዶ በመጐናጸፊያው ጠቅልሎ ቢይዝ፥ ልብሱም እንጀራና ወጥ፥ የወይን ጠጅና ዘይት ወይም ማናቸውንም ዐይነት ምግብ ቢነካ፥ ምግቡ ሁሉ በዚያ ሰው ምክንያት የተቀደሰ ሊሆን ይችላልን?” በላቸው፤ በዚህ መሠረት ነቢዩ ከጠየቃቸው በኋላ፥
ካህናቱ “የተቀደሰ ሊሆን አይችልም” ሲሉ መለሱ።
13ሐጌም እንደገና “ሬሳ በመዳሰስ የረከሰ አንድ ሰው፥ ከነዚህ የምግብ ዐይነቶች አንዱን ቢነካ፥ ያ የተነካው ምግብ በዕርግጥ ይረክሳልን?” ሲል ጠየቃቸው። #ዘኍ. 19፥11-22።
ካህናቱም “አዎ፥ ይረክሳል” ሲሉ መለሱለት።
14ሐጌም እንዲህ አለ፦ “ይህ ሕዝብ በሙሉ እንደዚያው ነው፤ ስለዚህ ሥራቸውና የሚያቀርቡት ቊርባን የረከሰ ነው” ይላል እግዚአብሔር።
ከእግዚአብሔር የተሰጠ የበረከት ተስፋ
15እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ምን እንደ ደረሰባችሁ አታስተውሉምን? እነሆ፥ ቤተ መቅደሱን መልሳችሁ መሥራት ከመጀመራችሁ በፊት፥ 16ሁለት መቶ ኪሎ እህል ለማግኘት ወደ ምርት ማከማቻው ሄዳችሁ፤ ነገር ግን ያገኛችሁት እህል አንድ መቶ ኪሎ ብቻ ነበረ፤ አንድ መቶ ሊትር የወይን ጠጅ ለማግኘት ፈልጋችሁ ወደ ወይኑ መጭመቂያ ሄዳችሁ፤ ነገር ግን ያገኛችሁት የወይን ጠጅ አርባ ሊትር ብቻ ነበረ፤ 17እናንተንና የሥራችሁን ውጤት ሁሉ በዋግ፥ በሌላም በተክሎች በሽታና በበረዶ መታሁ፤ ይህም ሁሉ ሆኖ ግን በንስሓ ወደ እኔ አልተመለሳችሁም። 18እነሆ ዘጠነኛው ወር ከገባ ከዛሬ ከኻያ አራተኛው ቀን ጀምሮ አስተውሉ፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሠረት ከተጣለበት ቀን ጀምሮ አስተውሉ። 19አሁን ለዘር የሚሆን እህል በጐተራ ባይኖር የወይንና የበለስ፥ የሮማንና የወይራም ተክል ሁሉ ገና ፍሬ ባይሰጥም ከዚህ ቀን ጀምሮ እኔ በረከትን እሰጣችኋለሁ።”
እግዚአብሔር ለዘሩባቤል የሰጠው ተስፋ
20በዚያው ወር በሃያ አራተኛው ቀን እግዚአብሔር እንደገና ለነቢዩ ለሐጌ ተናገረ። 21የይሁዳ ገዢ ለሆነው ለዘሩባቤል እንዲህ ብለህ ተናገር፦ “ሰማይንና ምድርን የማናውጥበት ጊዜ ይመጣል፤ 22በዚያን ጊዜ፥ የመንግሥታትን ዙፋን እገለብጣለሁ፤ ኀይላቸውንም እንዳልነበረ አደርጋለሁ፤ ሠረገላ ነጂዎችን ከነሠረገሎቻቸው እገለብጣለሁ፤ ፈረሶቻቸው ያልቃሉ፤ ፈረሰኞቻቸውም እርስ በርሳቸው ይጋደላሉ፤ 23አገልጋዬ ዘሩባቤል ሆይ! እኔ አንተን መርጬሃለሁ፤ አንድ ቀን መሪ እንድትሆን አንተን ለይቼ እንደ ማኅተም ቀለበቴ አደርግሃለሁ፤” ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
Currently Selected:
ትንቢተ ሐጌ 2: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997