ኦሪት ዘፍጥረት 7:1-11

ኦሪት ዘፍጥረት 7:1-11 አማ05

እግዚአብሔር ኖኅን እንዲህ አለው፤ “በዚህ ዘመን ካለው ትውልድ መካከል ጻድቅ አንተ ብቻ ሆነህ ስላገኘሁህ፥ ከመላው ቤተሰብህ ጋር ወደ መርከቡ ግባ። ንጹሕ ከሆኑት ወንዶችና ሴቶች እንስሶች ሁሉ ሰባት ወንድ፥ ሰባት ሴት ከአንተ ጋር ወደ መርከቡ አስገባ፤ ንጹሕ ካልሆኑት ወንዶችና ሴቶች እንስሶች ሁሉ ግን፥ አንድ ወንድ አንድ ሴት አስገባ። ከያንዳንዱ ዐይነት ወፍ ወንድና ሴት ሰባት ወንድ ሰባት ሴት አስገባ፤ ይህንንም የምታደርገው እያንዳንዱ ዐይነት እንስሳና ወፍ በሕይወት እንዲኖርና በምድር ላይ ለዘር እንዲተርፍ ነው። የፈጠርኩትን ሕያው ፍጡር ሁሉ ከምድር ገጽ ላይ ለማጥፋት ከሰባት ቀን በኋላ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሙሉ ዝናብ አዘንባለሁ።” ኖኅም እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ አደረገ። የጥፋት ውሃ በምድር ላይ በመጣ ጊዜ የኖኅ ዕድሜ 600 ዓመት ነበር። ኖኅ፥ ሚስቱ፥ ልጆቹና ሚስቶቻቸው ከጥፋት ውሃ ለማምለጥ ወደ መርከቡ ገቡ። ንጹሕ ከሆኑትና ካልሆኑት ከያንዳንዱ ዐይነት እንስሶች ወፎች፥ በደረታቸው እየተሳቡ ከሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶች ሁሉ ጥንድ ወንድና ሴት እየሆኑ፥ እግዚአብሔር ኖኅን ባዘዘውም መሠረት ወደ ኖኅ ወደ መርከቡ ገቡ። ከሰባትም ቀን በኋላ የጥፋት ውሃ በምድር ላይ መጣ። ኖኅ 600 ዓመት በሆነው ጊዜ፥ በሁለተኛው ወር በዐሥራ ሰባተኛው ቀን ላይ ከምድር በታች ያለው የታላቁ ውሃ ምንጮች ሁሉ በድንገት ተነደሉ፤ በሰማይ ያሉት የውሃ መስኮቶች ሁሉ ተከፈቱ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}