እግዚአብሔር በምድር ላይ ያሉ ሰዎች ሁሉ ምን ያኽል ዐመፀኞች እንደ ሆኑና ሐሳባቸውም ዘወትር ክፋት ብቻ እንደ ሆነ ተመለከተ፤ ስለዚህ ሰዎችን በመፍጠሩና በምድር ላይ እንዲኖሩ በማድረጉ አዘነ፤ እጅግም ተጸጸተ። በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር “እነርሱን በመፍጠሬ አዝኛለሁ፤ ስለዚህ እነዚህን የፈጠርኳቸውን ሰዎች፥ እንስሶችን፥ በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶችንና ወፎችንም ጭምር ከምድር ላይ አጠፋለሁ” አለ። ይሁን እንጂ ኖኅ የተባለው ሰው በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስን አግኝቶ ነበር። የኖኅ ታሪክ እንደሚከተለው ነው፤ ኖኅ በዘመኑ ምንም በደል የማይሠራና የእግዚአብሔርን መንገድ የሚከተል ደግ ሰው ነበር፤ ኖኅም ሴም፥ ካምና ያፌት የሚባሉትን ሦስት ወንዶች ልጆች ወለደ። በዚያን ጊዜ በምድር የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉዎች ነበሩ፤ ምድርም በዐመፅ ተሞልታ ነበር። እግዚአብሔር ዓለምን ተመለከተ፤ የተበላሸች እንደ ሆነችና በውስጧም ያሉት ሰዎች ሁሉ በክፋት እንደሚኖሩ አየ። እግዚአብሔር ኖኅን እንዲህ አለው፦ “የሰውን ዘር ለማጥፋት ወስኛለሁ፤ ምድር በሰዎች የዐመፅ ሥራ ስለ ተሞላች ሰዎችን ከምድር ጋር አጠፋቸዋለሁ፤ አንተ ግን ከጥሩ እንጨት መርከብ ሥራ፤ በውስጡም ብዙ ክፍሎች እንዲኖሩት አድርግ፤ መርከቡን ከውስጥና ከውጪ በቅጥራን ለቅልቀው። ርዝመቱን 133 ሜትር፥ የጐኑን ስፋት 22 ሜትር፥ የከፍታውን ቁመት 13 ሜትር አድርግ፤ ለመርከቡ ጣራ አብጅለት፤ ጣራውና ግድግዳው በሚጋጠሙበት ቦታ ላይ 44 ሳንቲ ሜትር ባዶ ቦታ ተውለት፤ መርከቡ ባለሦስት ፎቅ እንዲሆን አድርግ፤ በጐኑም በኩል በር አድርግለት፤ እነሆ፥ ከሰማይ በታች ሕይወት ያለውን ነገር ሁሉ ከምድር ላይ ለማጥፋት የጥፋት ውሃ አመጣለሁ፤ በምድር ላይ ያለ ሕያው ፍጥረት ሁሉ ይጠፋል። ከአንተ ጋር ግን ቃል ኪዳን እገባለሁ፤ አንተና ሚስትህ፥ ልጆችህና የልጆችህ ሚስቶች ወደ መርከቡ ግቡ። “ከአንተ ጋር በሕይወት እንዲጠበቁ ሥጋ ከለበሱ ሕያዋን ፍጥረቶች ከየዐይነቱ ሁለት ሁለት ወንድና ሴት እየወሰድህ ወደ መርከቡ አስገባ፤ በሕይወት እንዲኖሩ ከየዐይነቱ ወፎች፥ ከየዐይነቱ እንስሶች፥ በደረታቸው እየተሳቡ ከሚንቀሳቀሱ ከልዩ ልዩ ተንቀሳቃሽ ፍጥረቶች በየዐይነቱ ሁለት ሁለት ወደ አንተ ይምጡ። እንዲሁም ለአንተና ለእነዚህ ፍጥረቶች ሁሉ የሚበቃ ልዩ ልዩ ዐይነት ምግብ በመርከቡ ውስጥ አከማች።” ኖኅም እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ አደረገ።
ኦሪት ዘፍጥረት 6 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 6:5-22
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos