እግዚአብሔር አምላክ የሰው ዐመፅ በምድር ላይ የበዛና የልቡም ሐሳብ ዘወትር ወደ ክፋት ብቻ ያዘነበለ መሆኑን ተመለከተ። እግዚአብሔር ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፤ ልቡም እጅግ ዐዘነ። ስለዚህም እግዚአብሔር፣ “የፈጠርሁትን የሰው ዘር ከምድረ ገጽ አጠፋለሁ፤ ከሰው እስከ እንስሳ በምድር ላይ ከሚሳቡ ፍጥረታት እስከ ሰማይ ወፎች አጠፋለሁ፤ ስለ ፈጠርኋቸው ተጸጽቻለሁና” አለ። ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስን አገኘ። የኖኅ ታሪክ እንደሚከተለው ነው። ኖኅ በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች ሁሉ ይልቅ ጻድቅና ነቀፋ የሌለበት ሰው ነበር፤ አካሄዱንም ከእግዚአብሔር ጋራ አደረገ። ኖኅም ሴም፣ ካምና ያፌት የሚባሉ ሦስት ወንዶች ልጆች ነበሩት። ምድር በእግዚአብሔር ፊት በክፉ ሥራ ረከሰች፤ በዐመፅም ተሞላች። እግዚአብሔር ምድር ምን ያህል በክፉ ሥራ እንደ ረከሰች አየ። እነሆ፤ ሰው ሁሉ አካሄዱን አበላሽቶ ነበርና ስለዚህ እግዚአብሔር ኖኅን እንዲህ አለው፦ “ሰውን ሁሉ ላጠፋ ነው፤ ምድር በሰው ዐመፅ ስለ ተሞላች በርግጥ ሰውንም ምድርንም አጠፋለሁ። አንተ ግን በጎፈር ዕንጨት መርከብ ሥራ፤ ለመርከቧም ክፍሎች አብጅላት፤ ውስጧንና ውጭዋን በቅጥራን ለብጠው። እንዲህ አድርገህ ሥራት፦ ርዝመቷ መቶ አርባ ሜትር፣ ወርዷ ሃያ ሦስት ሜትር፣ ከፍታዋ ዐሥራ ሦስት ነጥብ ዐምስት ሜትር ይሁን። ለመርከቧ ጣራ አብጅላት፣ ጣራና ግድግዳው በሚጋጠምበት ቦታ ግማሽ ሜትር ክፍተት ተው፤ ከጐኗ በር አውጣላት፤ ባለሦስት ፎቅ አድርገህ ሥራት። እኔም ከሰማይ በታች የሕይወት እስትንፋስ ያለባቸውን ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ ለማጥፋት እነሆ፤ በምድር ላይ የጥፋት ውሃ አወርዳለሁ፤ በምድር ላይ ያለ ሁሉ ይጠፋል። ከአንተ ጋራ ግን ቃል ኪዳን እመሠርታለሁ። አንተና ወንዶች ልጆችህ፣ ሚስትህና የልጆችህ ሚስቶች ከአንተ ጋራ ወደ መርከቧ ትገባላችሁ። ከአንተ ጋራ በሕይወት እንዲቈዩ ከሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ ተባዕትና እንስት እያደረግህ ሁለት ሁለቱን ወደ መርከቧ ታስገባለህ። ከእያንዳንዱ የወፍ ወገን፣ ከእያንዳንዱ የእንስሳ ወገን፣ በምድር ላይ ከሚሳቡ ፍጥረታት ሁሉ በየወገናቸው በሕይወት ይቈዩ ዘንድ ሁለት ሁለት እየሆኑ ወደ አንተ ይመጣሉ። ለአንተና ለእነርሱ የሚያስፈልገውን ምግብ ሁሉ አከማች።” ኖኅም ሁሉን እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ።
ዘፍጥረት 6 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፍጥረት 6
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፍጥረት 6:5-22
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos