ኦሪት ዘፍጥረት 48:8-19

ኦሪት ዘፍጥረት 48:8-19 አማ05

ያዕቆብ የዮሴፍን ልጆች ባየ ጊዜ “እነዚህ ልጆች እነማን ናቸው?” ብሎ ጠየቀ። ዮሴፍም “እነዚህ እግዚአብሔር በዚህ አገር ሳለሁ የሰጠኝ የእኔ ልጆች ናቸው” ብሎ ለአባቱ መለሰለት። ያዕቆብም “እባርካቸው ዘንድ ወደ እኔ አቅርብልኝ” አለው። የያዕቆብ ዐይኖች በእርጅናው ምክንያት ስለ ደከሙ አጥርቶ ማየት አይችልም ነበር፤ ስለዚህ ዮሴፍ ልጆቹን ወደ እርሱ አቀረበለት፤ እርሱም ዕቅፍ አድርጎ ሳማቸው። ዮሴፍንም “አንተን እንደገና አያለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር፤ እግዚአብሔር ግን አንተን ብቻ ሳይሆን ልጆችህንም ጭምር አሳየኝ” አለው። ዮሴፍ ልጆቹን ከያዕቆብ ጒልበት ፈቀቅ አደረገና ወደ መሬት ጐንበስ ብሎ ሰገደ። ዮሴፍ ሁለቱን ልጆቹን ወስዶ ኤፍሬምን በቀኙ ለያዕቆብ በስተግራው በኩል፥ ምናሴን በግራው ለያዕቆብ በስተቀኝ በኩል አድርጎ አቀረበለት። ያዕቆብ ግን እጆቹን በማመሳቀል አስተላልፎ ቀኝ እጁን በታናሹ በኤፍሬም ራስ ላይ፥ ግራ እጁን በበኲሩ በምናሴ ራስ ላይ አኖረ። ከዚህ በኋላ ዮሴፍን እንዲህ ሲል ባረከው፦ “አባቶቼ አብርሃምና ይስሐቅ መንገዱን በመከተል ያገለገሉትና እኔንም ሕይወቴን ሙሉ እስከ ዛሬ ድረስ እረኛ ሆኖ የጠበቀኝ አምላክ እነዚህን ልጆች ይባርክ! እኔን ከጒዳት ሁሉ ያዳነኝ መልአክ እነርሱንም ይጠብቃቸው። የእኔ ስም፥ የአባቶቼም የአብርሃምና የይስሐቅ ስም በነዚህ ልጆች ሲታወስ ይኑር፤ ዘራቸውም በምድር ላይ ይብዛ።” ዮሴፍ አባቱ ቀኝ እጁን በኤፍሬም ራስ ማድረጉን ባየ ጊዜ ቅር ተሰኘ፤ ስለዚህ ከኤፍሬም ራስ ላይ አንሥቶ በምናሴ ራስ ላይ ለማኖር የአባቱን እጅ ያዘ፤ “አባቴ ሆይ፥ እንደዚህ አይደለም፤ በኲሩ ይህኛው ስለ ሆነ ቀኝ እጅህን በእርሱ ራስ ላይ አኑር” አለው። አባቱ ግን “ዐውቄአለሁ፤ ልጄ ዐውቄአለሁ፤ የምናሴም ዘር ታላቅ ሕዝብ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ የእርሱ ታናሽ ወንድም ከእርሱ ይበልጥ ታላቅ ይሆናል፤ ዘሮቹም ታላላቅ ሕዝቦች ይሆናሉ” አለ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}