የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘፍጥረት 48

48
ያዕቆብ ኤፍሬምንና ምናሴን እንደ ልጆቹ አድርጎ በመቀበል መባረኩ
1ጥቂት ጊዜ ካለፈ በኋላ “አባትህ ታሞአል” ተብሎ ለዮሴፍ ተነገረው፤ ስለዚህ ዮሴፍ ሁለቱን ልጆቹን ምናሴንና ኤፍሬምን ይዞ ያዕቆብን ለማየት ሄደ። 2ያዕቆብ ልጁ ዮሴፍ ሊጐበኘው መምጣቱን በሰማ ጊዜ ሰውነቱን አበረታቶ በመኝታው ላይ ተቀመጠ።
3ያዕቆብ ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “ሁሉን የሚችል አምላክ በከነዓን ምድር ሎዛ በምትባል ቦታ ተገለጠልኝ፤ ባረከኝም፤ 4ደግሞም ‘ዘርህን አበዛለሁ፤ ተወላጆችህም ብዙ ሕዝቦች ይሆናሉ፤ ይህችንም ምድር ከአንተ በኋላ ለሚመጡት ዘሮችህ ለዘለዓለም ርስት አድርጌ እሰጣቸዋለሁ’ አለኝ።” #ዘፍ. 28፥13-14።
5ያዕቆብ ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፤ “ልጄ ዮሴፍ እኔ እዚህ ከመምጣቴ በፊት በግብጽ ምድር የተወለዱልህ ሁለት ልጆችህ ከእንግዲህ የእኔ ልጆች ናቸው፤ ኤፍሬምና ምናሴ እንደ ሮቤልና እንደ ስምዖን ይቈጠራሉ። 6ከእንግዲህ ወዲህ ሌሎች ልጆች ቢወለዱልህ የአንተ ናቸው፤ ርስት የሚያገኙትም በኤፍሬምና በምናሴ ስም በመጠራት ይሆናል። 7ከመስጴጦምያ ስመለስ በከነዓን ምድር ገና ከኤፍራታ ሳልርቅ እናትህ ራሔል ሞተችብኝ፤ እርስዋን ወደ ኤፍራታ በሚወስደው መንገድ ዳር ቀበርኋት።” (ይህችም ኤፍራታ ዛሬ ቤተልሔም ተብላ የምትጠራው ቦታ ነች።) #ዘፍ. 35፥16-19።
8ያዕቆብ የዮሴፍን ልጆች ባየ ጊዜ “እነዚህ ልጆች እነማን ናቸው?” ብሎ ጠየቀ።
9ዮሴፍም “እነዚህ እግዚአብሔር በዚህ አገር ሳለሁ የሰጠኝ የእኔ ልጆች ናቸው” ብሎ ለአባቱ መለሰለት።
ያዕቆብም “እባርካቸው ዘንድ ወደ እኔ አቅርብልኝ” አለው። 10የያዕቆብ ዐይኖች በእርጅናው ምክንያት ስለ ደከሙ አጥርቶ ማየት አይችልም ነበር፤ ስለዚህ ዮሴፍ ልጆቹን ወደ እርሱ አቀረበለት፤ እርሱም ዕቅፍ አድርጎ ሳማቸው። 11ዮሴፍንም “አንተን እንደገና አያለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር፤ እግዚአብሔር ግን አንተን ብቻ ሳይሆን ልጆችህንም ጭምር አሳየኝ” አለው። 12ዮሴፍ ልጆቹን ከያዕቆብ ጒልበት ፈቀቅ አደረገና ወደ መሬት ጐንበስ ብሎ ሰገደ።
13ዮሴፍ ሁለቱን ልጆቹን ወስዶ ኤፍሬምን በቀኙ ለያዕቆብ በስተግራው በኩል፥ ምናሴን በግራው ለያዕቆብ በስተቀኝ በኩል አድርጎ አቀረበለት። 14ያዕቆብ ግን እጆቹን በማመሳቀል አስተላልፎ ቀኝ እጁን በታናሹ በኤፍሬም ራስ ላይ፥ ግራ እጁን በበኲሩ በምናሴ ራስ ላይ አኖረ።
15ከዚህ በኋላ ዮሴፍን እንዲህ ሲል ባረከው፦
“አባቶቼ አብርሃምና ይስሐቅ መንገዱን በመከተል ያገለገሉትና
እኔንም ሕይወቴን ሙሉ እስከ ዛሬ ድረስ እረኛ ሆኖ የጠበቀኝ
አምላክ እነዚህን ልጆች ይባርክ!
16እኔን ከጒዳት ሁሉ ያዳነኝ መልአክ
እነርሱንም ይጠብቃቸው።
የእኔ ስም፥ የአባቶቼም የአብርሃምና
የይስሐቅ ስም በነዚህ ልጆች ሲታወስ ይኑር፤
ዘራቸውም በምድር ላይ ይብዛ።”
17ዮሴፍ አባቱ ቀኝ እጁን በኤፍሬም ራስ ማድረጉን ባየ ጊዜ ቅር ተሰኘ፤ ስለዚህ ከኤፍሬም ራስ ላይ አንሥቶ በምናሴ ራስ ላይ ለማኖር የአባቱን እጅ ያዘ፤ 18“አባቴ ሆይ፥ እንደዚህ አይደለም፤ በኲሩ ይህኛው ስለ ሆነ ቀኝ እጅህን በእርሱ ራስ ላይ አኑር” አለው።
19አባቱ ግን “ዐውቄአለሁ፤ ልጄ ዐውቄአለሁ፤ የምናሴም ዘር ታላቅ ሕዝብ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ የእርሱ ታናሽ ወንድም ከእርሱ ይበልጥ ታላቅ ይሆናል፤ ዘሮቹም ታላላቅ ሕዝቦች ይሆናሉ” አለ። 20ስለዚህ በዚያን ቀን እንዲህ ሲል ባረካቸው፤ “እስራኤላውያን በሚመርቁበት ጊዜ የእናንተን ስም በማስታወስ፥ ‘እግዚአብሔር እንደ ኤፍሬምና እንደ ምናሴ ያድርጋችሁ’ ይላሉ።” #ዕብ. 11፥21።
በዚህ አኳኋን ያዕቆብ ኤፍሬምን ከምናሴ አስቀደመው።
21ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “እነሆ፥ እኔ የምሞትበት ጊዜ ተቃርቦአል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ነው፤ ወደ ቀድሞ አባቶቻችሁም ምድር ይመልሳችኋል፤ 22በሰይፌና በቀስቴ ከአሞራውያን እጅ የወሰድኩትን ለሙን ምድር ሴኬምን፥ ከወንድሞችህ ጋር ከምታገኘው ድርሻ በላይ ለአንተ ብቻ ሰጥቼሃለሁ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ