የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘፍጥረት 47:1-12

ኦሪት ዘፍጥረት 47:1-12 አማ05

ዮሴፍም ወደ ፈርዖን ሄዶ “አባቴና ወንድሞቼ በጎቻቸውንና ፍየሎቻቸውን ከብቶቻቸውንና ሌላም ያላቸውን ነገር ሁሉ ይዘው ከከነዓን ወደዚህ መጥተዋል፤ አሁንም በጌሴም ምድር ይገኛሉ” አለው። ከወንድሞቹ መካከል መርጦ ያመጣቸውንም አምስቱን ወንድሞቹን ወደ ፈርዖን አቀረባቸው። ፈርዖንም የዮሴፍን ወንድሞች፦ “የምትተዳደሩበት ሥራ ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም እንዲህ ብለው መለሱለት፥ “እኛ አገልጋዮችህ በግ አርቢዎች ነን፤ አባቶቻቸንም ይተዳደሩበት የነበረ ሥራ ይኸው ነበር። በከነዓን ምድር ራብ እጅግ ከመበርታቱ የተነሣ ለእንስሶቻችን ግጦሽ ስላጣን ለጊዜው በዚህች አገር ለመኖር መጥተናል፤ ስለዚህ አገልጋዮችህ በጌሴም ምድር እንድንኖር ፍቀድልን።” ፈርዖንም ዮሴፍን እንዲህ አለው፥ “አባትህና ወንድሞችህ ከመጡልህ፤ እነሆ፥ መላው የግብጽ ምድር የአንተ ነው፤ ስለዚህ አባትህና ወንድሞችህ ምርጥ በሆነችው በጌሴም ምድር እንዲኖሩ አድርግ። ከእነርሱ መካከል ልዩ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ካሉ፥ በእኔ እንስሶች ላይ የበላይ ኀላፊዎች አድርገህ ሹማቸው።” ከዚህ በኋላ ዮሴፍ አባቱን ያዕቆብን ወደ ፈርዖን አቀረበው፤ ያዕቆብም ፈርዖንን ባረከው፤ ፈርዖንም “ዕድሜህ ስንት ነው?” በማለት ያዕቆብን ጠየቀው። ያዕቆብም “በመንከራተት ያሳለፍኳቸው ዘመናት መቶ ሠላሳ ናቸው። እነርሱም የቀድሞ አባቶቼ በመንከራተት ካሳለፉአቸው ዘመናት እጅግ ያነሡና ችግር የበዛባቸው ናቸው” አለ። ያዕቆብ ፈርዖንን ባረከውና ተሰናብቶት ወጣ። ከዚህ በኋላ ዮሴፍ አባቱና ወንድሞቹ በግብጽ ምድር እንዲቀመጡ አደረገ፤ ፈርዖን ባዘዘው መሠረት በግብጽ ምድር ምርጥ የሆነውን፥ በራምሴ ከተማ አጠገብ ያለውን ቦታ በይዞታ ሰጣቸው። ዮሴፍ ለአባቱና ለወንድሞቹ በልጆቻቸው ቊጥር ልክ እህል ይሰጣቸው ነበር።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}