ኦሪት ዘፍጥረት 45
45
ዮሴፍ ማንነቱን ለወንድሞቹ መገለጡ
1ዮሴፍ የናፍቆት ስሜቱን በአገልጋዮቹ ፊት መቈጣጠር ባለመቻሉ “ሁላችሁም ከዚህ ውጡ” ብሎ አዘዘ፤ ስለዚህ ዮሴፍ ማንነቱን ለወንድሞቹ በገለጠ ጊዜ ማንም የውጪ ሰው በአጠገቡ አልነበረም። #ሐ.ሥ. 7፥13። 2በዚህ ጊዜ ግብጻውያን እስኪሰሙት ድረስ ድምፁን ከፍ አድርጎ አለቀሰ፤ የፈርዖንም ቤተሰብ ወሬውን ሰማ።
3ዮሴፍ ወንድሞቹን “እኔ ዮሴፍ ነኝ፤ አባቴ እስከ አሁን በሕይወት አለን?” አላቸው። ወንድሞቹ የተናገረውን በሰሙ ጊዜ እጅግ ደነገጡ፤ መልስ መስጠትም ተሳናቸው።
4በዚህ ጊዜ ዮሴፍ “እስቲ ወደ እኔ ቀረብ በሉ” አላቸው፦ ከቀረቡም በኋላ እንዲህ አላቸው፦ “እኔ ወደ ግብጽ የሸጣችሁኝ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ፤ 5ነገር ግን ይህን በማድረጋችሁ በመጸጸት አትበሳጩ፤ እግዚአብሔር እኔን አስቀድሞ የላከኝ የሰዎችን ሕይወት እንዳተርፍ ነው። 6በምድር ላይ ራብ ከገባ ሁለተኛ ዓመቱን ይዞአል፤ ሰዎች አርሰው መከር መሰብሰብ የማይችሉባቸው አምስት ዓመቶች ገና ይመጣሉ። 7እግዚአብሔር አስቀድሞ ወደዚህ የላከኝ በዚህ በአስደናቂ ዘዴ የእናንተን ሕይወት በማዳን በምድር ላይ ዘር እንዲቀርላችሁ አስቦ ነው።
8“ስለዚህ ወደዚህ የላከኝ ራሱ እግዚአብሔር እንጂ እናንተ አይደላችሁም፤ እግዚአብሔር ለፈርዖን እንደ መካሪ አባት፥ በቤት ንብረቱ ላይ ጌታና የመላው ግብጽ አገር ገዢ አደረገኝ። 9አሁን በፍጥነት ተመልሳችሁ ወደ አባቴ ሂዱና ልጅህ ዮሴፍ እንዲህ ይልሃል በሉት፤ ‘እግዚአብሔር የመላው ግብጽ ገዢ አድርጎኛል፤ ስለዚህ ሳትዘገይ ወደ እኔ ና፤ 10ልጆችህን፥ የልጅ ልጆችህን፥ በጎችህን፥ ፍየሎችህን፥ ከብቶችህን ሌላም ያለህን ነገር ሁሉ ይዘህ ና፥ በእኔው አቅራቢያ በሚገኘው በጌሴም ምድር ትኖራለህ። 11አምስት የራብ ዓመቶች ገና ስለሚቀሩ አንተና ቤተሰብህ እንስሶችህም ጭምር ራብ እንዳይደርስባችሁ በጌሴም እመግብሃለሁ።’ ” #ሐ.ሥ. 7፥14።
12ቀጥሎም ዮሴፍ እንዲህ አለ፤ “አሁን የምናገራችሁ እኔ ዮሴፍ መሆኔን እናንተና አንተም ወንድሜ ብንያም አይታችሁ ለማረጋገጥ ችላችኋል፤ 13በግብጽ አገር ያለኝን ታላቅ ክብርና ያያችሁትንም ሁሉ ለአባቴ ንገሩት፤ በፍጥነትም ወደዚህ አምጡት።”
14ከዚህ በኋላ የወንድሙን የብንያምን አንገት ዐቅፎ አለቀሰ፤ ብንያምም ወንድሙን ዐቅፎ አለቀሰ፤ 15ዮሴፍ የቀሩትንም ወንድሞቹን አንድ ባንድ እየሳመ አለቀሰ፤ ከዚህ በኋላ ወንድሞቹ ከእርሱ ጋር መነጋገር ጀመሩ።
16የዮሴፍ ወንድሞች መምጣት በፈርዖን ቤተ መንግሥት በተሰማ ጊዜ ፈርዖንና ባለሥልጣኖቹ ደስ አላቸው፤ 17ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፦ “ወንድሞችህ አህዮቻቸውን ጭነው ወደ ከነዓን እንዲመለሱ ንገራቸው፤ 18አባታቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ይዘው ይምጡ፤ እኔም በግብጽ አገር ለም የሆነውን ቦታ መርጬ እሰጣቸዋለሁ፤ በቂ ምግብ አግኝተው በደስታ መኖር ይችላሉ። 19እንዲሁም ሚስቶቻቸውን፥ ልጆቻቸውንና አባታቸውን አሳፍረው የሚያመጡበት ከግብጽ አገር ሠረገሎችን ይዘው እንዲሄዱ እዘዛቸው። 20በግብጽ ምድር ለም የሆነውን ቦታ ስለሚያገኙ ቤት ንብረታቸውን ትተው በመምጣታቸው ቅር አይሰኙ።”
21የያዕቆብ ልጆች ልክ እንደ ተነገራቸው አደረጉ፤ ዮሴፍም በንጉሡ ትእዛዝ መሠረት ሠረገሎችንና ለጒዞ የሚሆናቸውን ስንቅ ሰጣቸው፤ 22ለእያንዳንዳቸውም አንድ አንድ የክት ልብስ ሰጣቸው፤ ለብንያም ግን አምስት የክት ልብስና ሦስት መቶ ብር ሰጠው። 23ለአባቱም በዐሥር አህዮች የተጫነ ከግብጽ ምድር የሚገኘውን መልካም ነገር ሁሉ ላከለት፤ እንዲሁም በሚመጣበት ጊዜ ለስንቅ የሚሆነው በሌሎች ዐሥር እንስት አህዮች የተጫነ እህል፥ ዳቦና ሌላም ምግብ ላከለት። 24በዚህ ሁኔታ ወንድሞቹን ካሰናበታቸው በኋላ “በመንገድ አትጣሉ” ብሎ መከራቸው።
25የዮሴፍ ወንድሞች ከግብጽ ተነሥተው በከነዓን ወደሚኖረው አባታቸው ወደ ያዕቆብ ተመለሱ። 26እዚያም እንደ ደረሱ አባታቸውን “ዮሴፍ በሕይወት አለ፤ እንዲያውም በመላው ግብጽ ላይ አስተዳዳሪ ሆኖአል” አሉት። ያዕቆብ ግን እጅግ ደነገጠ፤ ሊያምናቸውም አልቻለም።
27ነገር ግን ዮሴፍ ያላቸውን ሁሉ በነገሩት ጊዜና እርሱን ወደ ግብጽ የሚወስዱበትን ዮሴፍ የላከለትን ሠረገላ ባየ ጊዜ ሕይወቱ በደስታ ታደሰ፤ 28ከዚህ በኋላ ያዕቆብ “ልጄ ዮሴፍ በሕይወት መኖሩን ካረጋገጥሁ ይበቃኛል፤ ከመሞቴ በፊት ሄጄ አየዋለሁ” አለ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 45: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997