ኦሪት ዘፍጥረት 44:18-34

ኦሪት ዘፍጥረት 44:18-34 አማ05

ይሁዳ ወደ ዮሴፍ ቀርቦ እንዲህ አለ፤ “ጌታዬ ሆይ፤ እባክህ አንድ ቃል እንድናገር ፍቀድልኝ፤ ምንም እንኳ የፈርዖንን ያኽል የተከበርክ ብትሆን እባክህ አትቈጣኝ። ጌታዬ ከአሁን ቀደም ‘አባት አላችሁ ወይ? ሌላ ወንድምስ አላችሁ ወይ?’ ብለህ ጠየቅከን፤ እኛም ‘ሽማግሌ አባት አለን፤ በስተርጅና የወለደውም ታናሽ ወንድም አለን፤ የልጁ ወንድም ሞቶአል፤ ከእናቱ ልጆች የቀረው እርሱ ብቻ ስለ ሆነ አባቱ በጣም ይወደዋል’ ብለንህ ነበር፤ አንተም ‘አየው ዘንድ ይዛችሁልኝ እንድትመጡ’ አልከን፤ እኛም ‘ልጁ አባቱን ትቶ መምጣት አይችልም፤ ትቶ ከመጣ ግን አባትየው መሞቱ የማይቀር ነው’ ብለን ለአንተ ለጌታችን ነግረንህ ነበር። ጌታችንም ለአንተ ለጌታችን ነግረንህ አገልጋዮቹን ‘ታናሽ ወንድማችሁን ይዛችሁ ካልመጣችሁ ዳግመኛ በፊቴ አትቀርቡም’ ብለህ በብርቱ አስጠነቀቅከን። “እኛም ወደ አባታችን በተመለስን ጊዜ ያልከንን ሁሉ ነገርነው፤ ከዚህ በኋላ እርሱ ‘አሁንም ወደ ግብጽ ተመለሱና ጥቂት እህል ሸምቱልን’ አለን። እኛም ‘ታናሽ ወንድማችን ከእኛ ጋር ካልሆነ በሰውየው ፊት መቅረብ አንችልም፤ ስለዚህ ወደዚያ መሄድ የምንችለው ታናሽ ወንድማችን ከእኛ ጋር የሄደ እንደሆን ብቻ ነው’ አልነው። አባታችንም እንዲህ አለን፤ ‘ሚስቴ ራሔል ሁለት ወንዶች ልጆች ብቻ እንደ ወለደችልኝ ታውቃላችሁ። ከእነርሱ አንዱ ከአሁን በፊት ተለይቶኛል፤ ከተለየኝ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ስላላየሁት ክፉ አውሬ በልቶት ይሆናል፤ አሁን ደግሞ ይህንን ወስዳችሁ በእርሱ ላይ አደጋ ቢደርስበት በእርጅናዬ ዘመን የምታመጡብኝ ሐዘን ወደ መቃብር ያወርደኛል።’ “አሁንም ብላቴናው ከእኛ ተለይቶ በመቅረት ወደ አገልጋይህ ወደ አባቴ ብንመለስ የብላቴናው ነፍስ ከእርሱ ጋር የታሰረች ስለ ሆነ፥ ብላቴናው ከእኛ ጋር እንደሌለ ሲያይ ይሞታል፤ እኛ አገልጋዮችህም የአገልጋይህን የአባታችንን ሽበት በሐዘን ወደ መቃብር እናወርዳለን፤ ከዚህም በላይ ስለ ልጁ ደኅንነት ራሴን ዋስ አድርጌ ለአባቴ ሰጥቼአለሁ፤ ደግሞም ‘ልጁን በደኅና መልሼ ባላመጣው በሕይወቴ ዘመን ሁሉ ተወቃሽ ልሁን’ ብዬ ቃል ገብቼለታለሁ። “ስለዚህ እኔ በልጁ ፈንታ የአንተ የጌታዬ ባሪያ ሆኜ እዚሁ ልቅር፤ ልጁ ግን ከወንድሞቹ ጋር ይመለስ፥ ልጁን ሳልይዝ እንዴት ወደ አባቴ መመለስ እችላለሁ? ይህን የመሰለ ከባድ ሥቃይ በአባቴ ላይ ሲደርስ ማየት አልችልም።”

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}